ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ስራ እድል ፈጠራ ፎረምና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

118
ጥቅምት 07/12  ኢዜአ  የስራ እድል ፈጠራን ማጠናከር በሚቻልበት ስልት ላይ ትኩረት የሚያደርገው 12ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ስራ እድል ፈጠራ ፎረምና አውደ ርዕይ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ከመጪው ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው ፎረምና አውደ ርዕይ በታዳጊ አገር ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነም ተገልጿል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄደው ፎረም የተዘጋጀው በብሪትሽ ካውንስል እና 'ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ'በተሰኘ ድርጅት ትብብር ነው። በፎረሙና አውደ ርእዩ ላይ በማህበራዊ ሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ 19 የእንግሊዝ ተቋማትን ጨምሮ ከኢትዮጵያና ሌሎች አገራት የተጋበዙ በርካታ ማህበራትና ተቋማት ይሳተፋሉ። "Local Traditions Fresh Perspectives" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን ፎረም በተመለከተ የብሪትሽ ካውንስል እና ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። ማህበራዊ የስራ ፈጠራ በተለያዩ መስኮች የሥራ እድልን በመፍጠር የዜጎችን ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ የንግድ ሞዴል ነው። የብሪትሽ ካውንስል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ፒተር ብራውን በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ እያደገ የመጣው ማህበራዊ የስራ እድል ፈጠራ ፍሬያማ እንዲሆን ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ መምከርና ተሳታፊዎች ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ ዋንኛ የፎረሙና አውደ ርዕዩ አላማ ነው ብለዋል። በፎረሙ ላይ አገራት በማህበራዊ ስራ ፈጠራ ያላቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ የፋይናንስ ስርአት፣ የህግ ማዕቀፎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። ፎረሙ በአፍሪካና በኢትዮጵያ ስኬታማ የሆኑ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ሰዎች ተሞክሯቸውን ለተሳታፊዎች የሚያቀርቡበት እድል የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የማህበራዊ የስራ ፈጠራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ መምጣቱንና እምቅ እድሎችም በመስኩ እንዳለ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በስኮትላንድ ኤደንብራ ከተማ በተካሄደ 11ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ስራ እድል ፈጠራ ፎረምና አውደ ርዕይ ላይ የዘንድሮውን አውደ ርዕይና ፎርም እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወሳል። ፎረሙንና አውደ ርዕዩን በኢትዮጵያ ለማካሄድ ያስፈለገበትም ምክንያት በአገሪቷ ያለውን የዘርፉን አቅም በማጎልበት ውጤታማ እንዲሆን ልምድና ተሞክሮ የሚገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው ሲሉም ሚስተር ፒተር ብራውን ገልፀዋል። ከአጠቃላይ ህዝቧ ከ70 በመቶ የሚልቀው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በሚገኝባት ኢትዮጵያ ውጤታማ የማህበራዊ ስራ እድል ፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ለማሳካት ፎረሙ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ አመልክተዋል። ብሪትሽ ካውንስል በኢትዮጵያ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ እንዲያድግ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ካውንስሉ በቀረጸው መርሃ ግብር በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማስተማር ተግባር እያከናወነ መሆኑን ነው ሚስተር ብራውን ያስረዱት። የክህሎት ስልጠና መስጠት፣ የገንዘብና ቴክኒክ ድጋፎችን ማድረግ፣ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ሰዎች እንግሊዝ ሄደው ያለውን ተሞክሮ እንዲያዩ የማድረግ ተግባር መከናወኑን በማከል። ባለፈው ዓመትም በካውንስሉ ድጋፍ ሶሻል ኢንተርራይዝ ኢትዮጵያ እንዲቋቋም መደረጉንም አውስተዋል። በኢትዮጵያ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ እንዲያድግ የእንግሊዝ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። የሶሻል ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትና የጠብታ አምቡላንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክብረት አበበ ማህበራዊ የሥራ ፈጠራ ወጣቶች ያላቸውን ክህሎት በመጠቀም በኢትዮጵያ ያሉትን ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ገቢ እንዲያገኙና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። ዜጎች እርዳታን ሳይጠብቁ የስራ ፈጣሪ በመሆን በዘላቂነት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑም መሳሪያ ይሆናል ብለዋል። ዜጎች የዘርፉ ጠተቃሚ ይሆኑ ዘንድ የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ፖሊሲ ማዘጋጀት፣ የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርአቶችን መዘርጋት እንዲሁም የግንዛቤ ስራ በስፋት ማከናወን ይገባል ሲሉም አቶ ክብረት አስገንዝበዋል። ከፖሊሲ አኳያ ብሪትሽ ካውንስል ኢትዮጵያና ሶሻል ኢንተርፕራዝ ኢትዮጵያ የማህበራዊ የስራ ፈጠራ ረቂቅ ፖሊሲ ማዘጋጀታቸውንና ረቂቁንም ከፎረምና አውደ ርዕዩ በኋላ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል። የማህበራዊ የስራ እድል ፈጠራ ትምህርት ተቀርጾ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊሰጥ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ለማህበራዊ የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲኖር መንግስትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በ12ኛው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ስራ እድል ፈጠራ ፎረምና አውደ ርዕይ ከ50 አገራት በላይ የተወጣጡ 1 ሺህ 200 የማህበራዊ የስራ ፈጠራ ተዋናዮች፣ መንግስትና የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች እንግዶች ይሳተፋሉ። ፎርምና አውደ ርዕዩ ከመካሄዱ በፊት ጥቅምት 10 እና 11 ቀን 2012 ዓ.ም ከኢትዮጵያና ከሌሎች ውጭ አገራት የተወጣጡ 100 ወጣቶች "የወጣቶች ፕሮግራም" በሚል የማህበራዊ ስራ ፈጠራ ስልጠና ይወስዳሉ። በፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ማህበራዊ የስራ ፈጠራ ባለሙያዎች ለወጣቶቹ ልምድና ተሞክሯቸውንም ያቀርባሉ። የብሪትሽ ካውንስል ኢትዮጵያና ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ የማህበራዊ የስራ ፈጠራ ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ 55 ሺህ ተቋማት እንዳሉ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም