በትግራይ 1 ሺህ 234 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል

65
ጥቅምት 07/12 መቀሌ ኢዜአ  በትግራይ ሃገር አቀፍ የደም ልገሳ ቀንን ምክንያት በማድረግ 1 ሺህ 234 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መዘጋጀቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በትግራይ ጤና ቢሮ የደም ባንክ ማእከላት አስተባባሪ አቶ ተክለወይኒ ሃይለ ለኢዜአ ዛሬ እንዳሉት ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓም የሚከበረው አገር አቀፍ የደም ልገሳ ቀንን ምክንያት በማድረግ በክልሉ በተቋቋሙ የመቀሌ፣አክሱምና ሁመራ የደም ባንክ ማእከላት አማካኝነት 1 ሺህ 234 ከረጢት ደም ለመሰብሰብ ታስቧል። የታሰበውን የደም መጠን ለመሰብሰብ እንዲቻልም በደም ባንክ ማእከላቱ ስር 11 ጊዜያዊ የደም መሰብሰቢያ ጣቢያዎች ይዘጋጃሉ ብለዋል ። ከፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚለገሰውን ደም የሚሰበስቡ የጤና ባለሙያዎች እንደሚዘጋጁ ገልፀዋል ። የክልሉ ህብረተሰብም ደም በመለገስ ሰብአዊነቱን በተግባር እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል ። የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሃይላይ ገብረስላሴ ቀኑን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት የደም ልገሳ ቀን መከበሩ ህብረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ በቀጣይነት የደም ልገሳ እንዲያደርግ መነሳሳት እንደሚፈጥር ያለውን እምነት ገልጿል። የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዕጻይ አብርሃ በበኩላቸው ለበርካታ ጊዜያት ደም እንደሚለግሱና ደም በመለገሳቸው ምክንያት ያስከተለባቸው የጤና ችግር አለመኖሩን ተናግረዋል። በመሆኑም ቀኑን ምክንያት በማድረግ በደም እጦት ምክንያት የሚቸገሩትን ህሙማን ለመታደግ ሁሉም ደም በመለገስ ወገኖቹን ሊታደግ ይገባል ብለዋል ። የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ባቋቋማቸው ሦስት የደም ባንክ ማእከላት አማካኝነት በዓመቱ 20 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ቀደም ሲል መገለጹ አይዘነጋም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም