በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፍን የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ... የኢትዮጵያ የእርቅ ሰላም ኮሚሽን

97
ጥቅምት 7/2012  በሀገሪቱ በህዝቦች መካከል የተዛቡ ግንኙነቶችን በማስተካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፍን ለተጀመሩ ስራዎች መሳካት የህዝቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ የእርቅ ሰላም ኮሚሽን አሳሰበ። የኮሚሽኑ አባላት ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ጋር በግጭት አፈታት ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት የኮሚሽኑ አባል የዓለም ሎሬት ዶክትር ጥበበ የማነብረሃን እንዳሉት በሀገሪቱ የተለያዩ ጊዜያት ተፈጥረው የነበሩት  ግጭቶች የተዛቡ ግንኙነቶችንና ትረክቶችን ያለ ህዝቡ ተሳትፎ በኮሚሽኑ ብቻ ውጤታማ ሊሆኑ አይችልም። እነዚህን ችግሮች  በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን  ከህዝቡ ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። "አባቶች ያቆዩትን የአንደነትና አብሮነት እሴት በመውሰድ ዘላቂ ሰላም የተረጋገጠባት ሀገር ለትውልዱ ለማስረከብ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል "ያሉት ደግሞ ሌለው የኮሚሽኑ አባል አባገዳ ጉበና ሁሉና ናቸው። አባ ገዳው እንዳመለከቱት የአባቶችነን   የግጭት አፈታትና የእርቅ ስነ- ስርዓት እሴቶችን የመጠቀሙ ባህል ሊዳብርም  ይገባል። የኮሚሽኑ አባል አቶ አባተ ኪሾ በበኩላቸው  እያንዳንዱ ማህበረሰብ በተለይም የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ስለ ሰላም በመስበክ ችግሮቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የኮሚሽኑ አባላት አሳስበዋል። የኮሚሽኑ አባላት ወደ ጋምቤላ የመጡት ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶችን ለይተው በግብዓትነት ለመጠቀም እንደሆነም አመልክተዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሞድ ኡጁሉ  እንደተናገሩት በኮሚሽኑ ለተጀመሩት የሰላም ስራዎች መሳካት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን  ድጋፍ ያደርጋል። በተለይም ለተጀመሩት የሰላም ስራዎች በግብዓትነት የሚግዙ መረጃዎችን ማቀበል ብቻ ሳይሆን የክልሉ የሀገር ሽማግሌችና የኃይማኖት አባቶች ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ጭምር  ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች  ነዋሪዎች መካከል አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም በሰጡት አስተያየት ለተጀመረው የሰላም ግንባታሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማደረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ግጭትን ለፈጥሩ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት አስቀድሞ በመፍታት ለአካባቢያቸው ሰላም ለመስራት ዝግጁ መሆናውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አሸኔ አስተኒ ናቸው።     በጋምቤላ ከተማ ትናንት በተካሄደው ውይይት የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና  የከተማው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ዙሪያ መክረዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም