የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች በተሟላ መልኩ ሊተገበሩ ይገባል - የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት

120
መቀሌ ሰኔ 11/2010 አገሪቱ የጀመረችውን ፈጣን እድገት ዘላቂ ለማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች በተሟላ መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስታወቁ፡፡ 264 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የራያ ዩኒቨርስቲ ትናንት ተመርቋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአገሪቱ እድገት ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማረጋገጥ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ባለድርሻ አካላትም ለትምህርት ጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች ትግበራ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ዶክተር ሙላቱ አሳስበዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው የራያ ዩኒቨርስቲ የተገነባው የከፍተኛ ትምህርትን ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ነው ያሉት፡፡ “ዩኒቨርስቲው በምርምርና ጥናት ይበልጥ እንዲታወቅና የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት በትኩረት መስራት አለበት'' ብለዋል፡፡ “ዩኒቨርስቲው  ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የሃገሪቱን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ለማሟላት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት የሚያስችለውን ግብና አቅጣጫ ተከትሎ ወደ ስራ ገብቷል'' ሲሉም ገልፀዋል፡፡ “በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ፀጋ በምርምርና ጥናት ይበልጥ እንዲጎለብት ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ መልካም እድል ነው''  ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ የአምባአላጀ ታሪካዊ ስፍራና በክልሉ በርዝመቱ የሚታወቀው የ“ፅበት’’ ተራራ፣ የሓሸንጌ ሃይቅ፣ የሕጎምብርዳና የግራካህሱ የተፈጥሮ ጥብቅ ደኖች፣  ለምርምርና ጥናት የሚሆኑ ቦታዎች መኖራቸው በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ “ራያ ዩኒቨርስቲ  በትግራይ ደቡባዊ ዞን የሚገኙ የቱሪዝም ፀጋዎችን፣ እምቅ ባህላዊ እሴቶችን በማጥናትና በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ትልቅ የቤት ስራ አለበት’’ብለዋል ፡፡ የሌሎች ዩኒቨርስቲዎች መልካም ተሞክሮዎችን በመቅሰም ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኑ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው “ሳይንስ ለተሻለ ህይወት’’ በሚል መሪ ቃል  "የማህበረሰብ ኑሮን ማሻሻል ትኩረቱ አድርጎ መደበኛ ስራውን  በይፋ ጀምሯል’’ ብለዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም