በደቡብ ክልል የሚነሱ የመዋቅር ጥያቄዎች በጥቂት ፖለቲከኞችና ባለሃብቶች ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ናቸው

118
ሀዋሳ ኢዜአ ጥቅምት 06/2012 በደቡብ ክልል ለሁከት መንስኤ እየሆኑ የሚገኙት የመዋቅር ጥያቄዎች ለህብረተሰቡ ከሚያመጡት ጠቀሜታ ይልቅ በጥቂት ፖለቲከኞችና ባለሀብቶች ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት የክልሉ ምክር ቤት በ2011 በጀት አመት አፈፃፀም ላይ በተወያየበት ወቅት ነው ፡፡ አቶ ርስቱ እንደገለፁት በክልሉ የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ክልሉን በተለያዩ አቅጣጫዎች ችግር ውስጥ ከተውታል ፡፡ ህዝቡ ያሉበት ችግሮች እንዲፈቱለት መጠየቁ አግባብ እንደሆነ የገለፁት አቶ ርስቱ በተለይ ከመዋቅር ጥያቄዎች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል አቋም የሚመሩ በመሆናቸው ለግጭትና ሁከት መንስኤ እየሆኑ ይገኛሉ ፡፡ ይህም ለፀረ-ሠላም ኃይሎች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ” መዋቅር ሲፈቀድ ጥቂቶች ወንበር ይሞቃቸዋል እንጂ ህዝብ የሚያገኘው ቤሳቤስቲን የለም”  ፡፡ በክልሉ እየተነሱ ያሉ ጥቄዎች ለህዝቡ ሊያመጡ ከሚችሉት ጠቀሜታ ይልቅ በጥቂት ፖለቲከኞችና ባለሀብቶች ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ዋጋ እያስከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ላይ ሰከን ብሎ ማሰብና መወያየት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል ፡፡ ባጋጠሙን የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የግል ኢንቨርስትመንት እየሸሸን ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት መመሪያዎችንና አሠራሮችን የመፈተሸ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ  የማስተካከያ እርምጃዎችንም እንደሚወስዱ አስረድተዋል ፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ አካባቢውን ለኢንቨስተሮች ምቹ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል ነው ያሉት ፡፡ በአሁን ሰዓት የደቡብ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮን እየመሩ የሚገኙት አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው በ2011 ዓም አብዛኛው የክልሉ አመራር አካላት ጊዜያቸውን ያጠፉት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስና መልሶ በማቋቋም ሥራ ተጠምደው  እንደነበር አስረድተዋል ፡፡ በአሁን ሰዓት ወደ ቀያቸው ያልተመለሱ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ኤልያስ የክልሉ መንግስት ትኩረት በመስጠት የካፒታል ፕሮጀክቶችንና መጠባበቂያ በጀቶችንም ጭምር በማጠፍ ተፈናቃዮችን የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሥራዎችን መከናወኑን አብራርተዋል ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች የሚፈናቀሉት ከጉዳዩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ፣ ሕፃናትና አዛውንቶች መሆናቸውን ገልፀው አንዱ ሌላውን በማፈናቀል ሊፈረጅ የሚችልም አንድም ብሔር እንደሌለ ተናግረዋል ፡፡ ነገር ግን የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላት በመደራጀት የሚፈፅሙት ተግባር እንደሆነ ገልፀው ለሚፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል ፡፡ አቶ ኤልያስ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናቶችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት ፡፡ ግጭቶች ውስጥ እጃቸውን በማስገባት የሚጠረጠሩ አመራሮች ፣ የፀጥታ አካላትና ሌሎች ተዋናዮችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከህብረተሰቡ ጋር መስራት እንደሚገባ ገልፀው በአሁን ሰዓት ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል ፡፡ ዕርቀ ሠላም የማውረድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራውም ዕቅድ ወጥቶለት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል:: በክልሉ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለግጭትና ሁከት መነሻ እየሆኑ ካሉ ጉዳዮች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከአደረጃጀትና ከወሰን ማካለል ጋር የተያያዙ ናቸው ያሉት አቶ ኤልያስ  በክልሉ ዝግ ሆኖ የቆየውን የአደረጃጀት ጉዳይ ለመመለስ በተሰራው ሥራ አራት ተጨማሪ ዞኖችና 50 አዳዲስ ወረዳዎችን መፍጠር መቻሉት አስረድተዋል ፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን ለማስተዳደር አቅም ያጠራቸው አዳዲስ መዋቅሮች ተመልሰው ችግር ውስጥ እየገቡ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት ፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሪት ደስታ አለንጎ እንደተናገሩት ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች አንድነታችንን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች ተፈጥረዋል ብለዋል ፡፡ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፈታት የተሄደበት መንገድ አበረታች እንደሆነ የተናገሩት ወይዘሪት ደስታ ሆኖም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል  ፡፡ አንድነትን የሚያጠናክሩ እሴቶችን ለማጎልበት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው የሠላም እሴት ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ አለመሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግጭቶች ከተከሰቱና የዜጎች ሕይወት ከጠፋ በኃላ የማረጋጋት ተግባራት እንደሚከናወኑ የገለፁት ወይዘሮ ሂክማ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የቅድመ መከላከል ሥራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም