አቀባበሉ ትምህርታቸውን ያለስጋት ለመጀመር እንዳነሳሳቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ

39
ሆሳዕና/ ደሴ /ሶዶ ኢዜአ ጥቅምት 6 ቀን 2012  የተደረገላቸው አቀባበል ትምህርታችንን ያለስጋት ለመጀመር ያነሳሳቸው መሆኑን በወራቤና ደሴ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ። ዩኒቨርሲቲዎቹ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል አድርገዋል። ከባህር ዳር ወደ ወራቤ ዩኒቨርሲቲ የመጣው  ተማሪ ዳምጤ ላንክር ለኢዜአ እንደገለፀው ዩኒቨርሲቲውን ሲቀላቀል የተደረገለት አቀባበል አስደስቶታል። "የተደረገልኝ አቀባበል ትምህርቴን ያለስጋት እንድጀምር አነሳስቶኛል" ያለው ተማሪው  በቆይታው ትምህርቱ ላይ በማተኮር ዓላማውን ለማሳካት እንደሚጥር ገልጿል። ከአሰላ የመጣችው ተማሪ ትዕግስት እርሳሷ በበኩሏ የተደረገላቸው አቀባበል ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ማድረጉን ተናግራለች ። ለትምህርቷ ትኩረት በመስጠት ለመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊነት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ አመለክታለች። በስልጤ ዞን እስልምና ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሙዘይን ሼህ ሰይድ "ተማሪዎች ሰላማቸው ተጠብቆ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል የዩኒቨርሲቲው ኘሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር ቶፊቅ ጀማል  የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እዲሆን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው አዲስ የተመደቡለትን 1ሺህ 750 ተማሪዎች መቀበሉን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ከደቡብ ክልል ወደ ደሴ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ የመጣችው ተማሪ ጸጋነሽ አበራ "የተደረገልን አቀባበል የደሴን የፍቅር፣ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌትነት አሳይቶናል"ብላለች። አቀባበሉ  ትምህርቷን ያለስጋት እንድትጀምር እንዳበረታታት ተናግራች ። "የተደረገልን አቀባበል ኢትዮጵያዊ አንድነት፣ፍቅርና ሰላምን ያሳያል ነው" ያለው ደግሞ ከኦሮሚያ የመጣው ተማሪ አማና ዱሪ ነው ። በቆይታው ለትምህርቱ ትኩረት በመስጠት የመጣበትን የትምህርት ዓላማ ለማሳካት ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጿል። የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት አሊ ይመር ከዩኒቨርሲቲውና ከከተማው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በተማሪዎች አቀባበል ላይ መሳተፉን ተናግሯል። የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ  ዩኒቨርሲቲው የተመደቡለትን 4ሺህ 287 አዲስ ተማሪዎች መቀበሉን አመልክተዋል። ተማሪዎችን የተቀበሉት ዩኒቨርሲቲው አውቶቡሶችን ደሴና ኮምቦልቻ መናኽርያዎች በመመደብ  እንደሆኑ አስረድተዋል። እንደ ዶክተር መንገሻ ገለጻ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊነት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ዝግጅት ተደርጓል። በተመሳሳይ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውንና  ለትምህርታቸው ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ  የመማር ማስተማር ስራ ውጤታማ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው  እስከ አዲስ አበባ ተሽከርካሪዎችን በመላክ ተማሪዎችን መቀበሉን አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው  ዘንድሮ 3ሺህ አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም