ኢትዮ-ቴሌኮም በሩብ ዓመቱ በውጭ ምንዛሬ ከሚሰጡ አገልግሎቶች 41 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር አገኘ

98

ኢዜአ፤ ጥቅምት 6/2012 ኢትዮ-ቴሌኮም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በውጭ ምንዛሬ ከሚሰጡ አገልግሎቶች 41 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ገለጸ።  በሩብ ዓመቱ 10 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።

ቴሌኮሙ በዘርፉ ሊደረግ በታሰበው ለውጥ ውስጥ ብቁ ፣ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የመስሪያ ቤቱን የ2012 መጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃጸም ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2011 ዓ.ም የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን ሲያደርግ በመቆየቱ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ስራ አፈፃፀሙ ውጤት ማምጣት መቻሉን አመልክቷል።

''ተቋሙ በዚሁ ወቅት የሰበሰበው ገቢ የእቅዱን 98 በመቶ ለማሳካት የቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 56 በመቶ የሚሆነው ከድምጽ አገልግሎት የተገኝ ነው'' ብለዋል።

ቀሪው ደግሞ ከሞባይል ዳታ መገኘቱን አመልክተው በውጭ ምንዛሪ ከሚሸጡ አለም አቀፍ አገልግሎቶችም  41 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን አስረድተዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 21 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ የኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 44 ነጥብ 4 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የደንበኞች ቁጥርም 10 በመቶ መጨመሩንም አንስተዋል።

ቴሌኮሙ በለውጡ ሒደት አገርና ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግና የተሻለ አፈፃፀም አስመዘግቦ ተመራጭ በሚያደርጉት መስኮች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት  የቴሌኮሙን አገልግሎት የሚጋሩ ሁለት ኩባንያዎች ከውጭ እንዲገቡ በመንግስት የተወሰነ በመሆኑ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ከወዲሁ አቅሙን የማሳደግ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥም የአደረጃጀት፣ የክሕሎት፣ የብቃት፣ የጥራትና የኔትወርክ ማስፋፊያ ስራዎች የሚገኙበት ሲሆን በእነዚህ ተግባራቱ የተሻለ ማድረጉ ተመራጭ እንደሚያደርገው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

መንግስት የቴሌኮም ዘርፉ ላይ ያስቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል።

''ከእለት ተለት የኦፕሬሽን ስራዎች ጎን ለጎን ከሚመጡት ኩባንያዎች ጋር ለመወዳደርና ራሳችንን ብቁ አድርገን ለመቅረብ የኔትወርክ ማስፋፋትና የአገልግሎት ጥራት ላይ እየሰራን ነው'' ሲሉም ጠቁመዋል።

ኩባንያዎቹ ተወዳድረው ወደ ስራ ለመግባት የሚወስድባቸውን ጊዜ እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም        ኢትዮ-ቴሌኮም የበለጠ ተሻሽሎ ተመራጭ ለመሆን እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማጠናከርና ተወዳዳሪነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ያስችለኛል ያለውን የሶስት  ዓመት አዲስ ስትራቴጂ “ብሪጅ” በሚል ስያሜ ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ፣ የአገልግሎት፣ የቴክኖሎጂና ኦፕሬሽን ልህቀትን መፍጠር፣ እንዲሁም የሰው  ኃይል ልማት ተኮር ተቋም መገንባትና ምርጥ የሆኑ ሁለንተናዊ ተሞክሮዎችን መጠቀም የስትራቴጂው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

በወቅቱም በ2012 በጀት ዓመት የደንበኞችን ብዛት በ16 በመቶ በማሳደግ የተጠቃሚውን ቁጥር ወደ 50  ሚሊዮን ለማሳደግና አጠቃላይ ገቢውን 45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም