አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው … የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው … የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን

ኢዜአ፤ ጥቅምት 6/2012 በተያዘው በጀት ዓመት የበጋ ወራትን ጨምሮ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገልጿል።
በኮሚሽኑ የአነስተኛና ሰፋፊ የደን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይንሐረግ ትግሉ እንዳሉት ኮሚሽኑ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በየዓመቱ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዶ ሲንቀሳቀስ ነበር።
ኮሚሽኑ በየዓመቱ ባቀደው መሰረት እያሳካ ባይሄድም ባለፈው ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ቀን በተደረገው ርብርብ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ ሳቢያ በአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሀምሌ 22 ቀን 2011 በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ አሻራ ቀን ብቻ ከ 366 ሚሊየን በላይ ችግኞች በ122 ሺህ 885 ሄክታር ላይ መተከሉን ያነሱት ዳይሬክተሯ ይህ አይነቱ ተሳትፎና ትብብር በተያዘው ዓመት ተጠናክሮ ከቀጠለ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ሊተከሉ ይችላሉ ነው ያሉት።
ለችግኝ የሚሆኑ ዘሮች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የዳሰሳ ስራ መከናወኑን ጠቁመው፤ በዳሰሳውም የችግኝ ጣቢያዎች በየአካባቢው በጥሩ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙና የችግኝ ተከላውና የማፍላት ስራው እንደየአካባቢው ስነምህዳር ይለያያል ብለዋል።
እርጥበታማና ደረቃማ አካባቢዎች እንደየ አካባቢያቸው ባህሪያት በተለያዩ ወቅቶች ተከላ እንደሚከናውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ በአንቆርጫ የደን ማእከል የደን ዛፍ ሲንከባከቡ ያገኘናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለችግኝ ተከላ ያለው ተነሳሽነት በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም በእንክብካቤው ረገድ ግን ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።
በዚሁ አካባቢ ነዋሪ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ደጀኔ ለገሰ በክረምት የተከላቸውን ችግኞች በአቅራቢያው የሚገኙ በመሆናቸው ብዙም እንደማይቸግረው ጠቁሞ፤ ውሃ በማጠጣትና በመኮትኮት እየተንከባከበ መሆኑን ጠቅሷል።
እዚሁ አካባቢ በየጊዜው እየመጡ የተከሏቸውን ችግኞች የሚንከባከቡ ጥቂት ነዋሪዎች ና የተቋማት ሰራተኞች መኖራቸውን የጠቀሰው ወጣት ደጀኔ፤ በርካታ ተቋማት ግን ተክለው ከሄዱ በኋላ አብዛኛው ችግኝ በእንክብካቤ ማጣት ሳይጸድቅ እንደሚቀር ጠቁሟል።
በአንቆርጫ ደን ማዕከል በጥበቃ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ሞገስ ቢልጫ በበኩላቸው የተተከሉትን የደን ችግኞችን በርካታ ወጣቶች ወደ ስፍራው እየመጡ እየተንከባከቡ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በሌላ በኩል በመሥሪያ ቤቶች አማካኝነት የተተከሉትን ችግኞች የሚንከባከቡ ተቋማት እንዳሉ ሁሉ ከተተከሉ በኋላ ተመልሰው የማያዩ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ችግኞቹ እንዲጸድቁ ህብረተሰቡ ሊንከባከባቸው እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።