የወሎ ጋቢና የደሴ ሳፋ ደረጃ ወጣላቸው

164

ደሴ ኢዜአ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም…. የደቡብ ወሎና አካባቢው መለያ የሆኑ ምርቶችንና የእደ ጥበብ ውጤቶችን ደረጃ እንዲሰጣቸው በማድረግ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ ።

ዩኒቨርሲቲው የወሎ ጋቢ እና የደሴ የብረት ሳፋ ላይ ጥናት በማካሄድ በኢትየጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በማስመዝገብ ደረጃ እንዲያገኙ አድርጓል።

በዩኒቨርሲቲው የብራንዲንግ አስተባባሪ አቶ አንዳርጋቸዉ አበበ እንደገለጹት በወሎ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶች ደረጃ አግኝተው አምራቹ ማህበረሰብ በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው።

የወሎ ጋቢ፣ የደሴ የብረት ሳፋ፣ የወሎ ጭስና የወረባቦ ብርቱካን ደረጃ ለማሰጠት የትና እንዴት ይመረታሉ ፣የጥራትና የምርታቸው ብዛት ምን ይመስላል የሚለውን ለማወቅ ለአራት ዓመታት ጥናት ተካሂዷል።

በዚህም የወሎ ጋቢ በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ስር በሚገኙ ወረዳዎችና በደሴና ወልድያ ከተሞች የሚመረት ሲሆን የደሴ የብረት ሳፋ ደግሞ ደሴ ከተማ ላይ ብቻ በብዛት መመረቱን በጥናት ተረጋግጧል።

ጥናቱንና ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎቸን ለኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በማቅረብም ለሁለቱ ምርቶች በመስከረምን ወር ተመዝግበው ደረጃ እንዲወጣላቸው ተደርጓል ብለዋል።

ሌሎቹ ምርቶችም በቀጣይ በማስመዝገብ የባለቤትነት ማረጋገጫ ለማግኘትና ደረጃ እንዲሰጣቸው የሚያስችል ማስረጃዎች መቅረባቸውን አውስተዋል።

ምርቶቹንና የእደ ጥበብ ውጤቶችን በማስመዝገብ  ደረጃ እንዲያገኙ በማድረግ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት በዋጋ የመደራደርንና የአምራቾችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም  አምራቾች ለህዝብ እይታ ምቹ የሆኑ መሸጫና መስራያ ቦታም እንዲያገኙ ከደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ መላኩ ሚካኤል በበኩላቸው የአካባያቸው ምርቶችና የእደ ጥበብ ውጤቶች በአገር አቀፍና በውጪው ዓለም እንዲተዋወቁ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተጀመረው ስራ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል ።

የወሎን የፍቅር፣ የአንድነትና የመቻቻል እሴቶችን በሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

ደረጃ በሚያገኙ ምርቶችና የእደ ጥበብ ውጤቶች ለማቅረብ ለሚሰሩ አካላት ምቹ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ለማመቻቸትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

ከተማ አስተዳደሩ ለዘርፉ ድጋፍ በማድረግ ወጣቶችን አደራጅቶ በማሰማራት ለስራ እድል ፈጠራ ለመጠቀምም እቅድ እንዳለዉም ገልጸዋል፡፡

ወጣት ሁሴን ይመር እንደገለጸው 20 ሆነው በመደራጀት በደሴ ከተማ የደሴ የብረት ሳፋ በተለያየ መጠን እያመረቱ ይገኛሉ።

ለ10 አመታት ቢያመርቱም በህገ ወጥ ደላሎች በልፋታቸዉ ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናግሯል፡፡

አሁን ምርታቸው በኢትየጵያ አአምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተመዝግቦ ደረጃ በማግኘቱ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው የገለጸው ፡፡

በቀን እስከ 500 የአፈር መዛቂያና የልብስ ማጠቢያ የብረት ሳፋ እንደሚያመርቱ ጠቁሞ በጥራትና በብዛት በማምረት በቀጥታ ለተጠቃሚው ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግሯል።

የወሎ ጭስና የወረባቡ ብርቱካንም በቅርቡ ብራንድ እንዲያገኝ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ መሆኑ ታውቋል።