ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ ችግኝ ጣቢያዎች ተለይተዋል

89
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 6/2012 በዓመቱ መጨረሻ ለሚተከለው አምስት ቢሊዮን ችግኝ ከሁለት ሺህ በላይ የችግኝ ጣቢያዎች መለየታቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አምስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ የበጀት ዓመቱን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ማቅረባቸው ይታወሳል። ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር እንደሚከናወን ገልጸዋል። ኢዜአ ዘንድሮው ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የደን ጥምር እርሻ ባለሙያን አቶ መስፍን ገብረዮሐንስን አነጋግሯል። አቶ መስፍን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ መጀመራቸውንና ለችግኝ ተከላው የሚሆኑ ጣቢያዎች የመለየት ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል። በመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በአርሶ አደሮች እና በሌሎች ተቋማት የሚተዳደሩ የችግኝ ጣቢያዎች እየተለዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች እስከ ሁለት ሺህ 300 የችግኝ ጣቢያዎች መለየታቸውን ተናግረዋል። ችግኝ ጣቢያዎችን የመለየት ተግባርም በዚህ ወር ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንም አመልክተዋል። ከችግኝ ጣቢያዎች ልየታው በተጨማሪ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለማፍላት በቂ መሆናቸውን የመፈተሽ ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል። ለችግኝ ዘር የሚውል ስምንት ሚሊዮን ብር ከመንግስት ለክልሎች እንደተሰጠና በክልሎች አቅም ሊሟሉ የማይችሉ ጉዳዮችን በመለየት ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል። በቀጣይ ቀናትም ያለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ ያለበትን ደረጃና ለዘንድሮው ዓመት የችግኝ ተከላ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ በባለሙያዎች የመስክ ምልከታ ይደረጋል ነው ያሉት። ለዘር የሚሆኑ ዛፎች ያሉበትን ቦታ መለየት፣ የችግኝ ዘሩን ጥራት መጠበቅ፣ ለችግኝ ተከላው የሚያስፈልግ ቁሳቁስ የማደራጀትና የማሟላት፣ ችግኝ የማፍላት፣ ለችግኝ ተከላው በቂ ባለሙያ መመደብና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሆኑም ነው አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል። በ2011 ዓ.ም ለአራት ቢሊዮን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የተቋቋመው ብሔራዊ አስተባባሪ አሁን የጀመረውን ስራ በተያዘው ዓመትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት የተተከሉ ነባር የችግኝ ዝርያዎች ዘንድሮም እንደሚተከሉ አስታውቀዋል። ለደን ጥምር እርሻ፣ ደን ልማት፣ መኖና ፍራፍሬ የሚሆኑ የችግኝ ዛፎች እንደሚዘጋጁም ገልጸዋል። አሁን የተጀመረው ስራ ለቀጣይ ሶስትና አራት ዓመታት በዘላቂነት ከተሰራና የእንክብካቤው ስራ በተቀናጀ መልኩ ከተከናወነ በደን ልማት ተጨባጭ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልም እንዲሁ። በተያዘው እቅድ መሰረት የ2012 ዓመት የችግኝ ተከላ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም