የካይዘን አሰራርን የበለጠ ለማስፋት እየተሰራ ነው … የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት

1933

መቐሌ /ኢዜአ/ ጥቅምት6 /2012 ኢትዮጵያ ውስጥ በ750 መንግስታዊና የግል ተቋማት የተጀመረውን የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ወደ ሌሎች ተቋማት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ገለፁ ።

ባለፉት ሁለት ቀናት በካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በመቀሌ ከተማ  ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ያኢ እንደገለፁት የኮንፈረንሱ ዓላማ በሃገሪቱ በ750 መንግስታዊና የግል ተቋማት ውጤታማ የሆነው የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና አሰራር ወደ ሌሎች ተቋማት ለማስፋት ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ የካይዘን ፍልስፍናና ያስገኘው ውጤት፤ የካይዘን የልማት ቡድን አደረጃጀት፤ ካይዘን የሃብትና ንብረት ብክነትን ለመቀነስ የሚጫወተው ሚና የሚሉና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የካይዘን ስራ አመራር ፍልስፍና ተግባራዊ ያደረገችው ጃፓን አሁን የግዙፍ ኩባንያዎች ባለቤት ከሆኑ የዓለም ሃገራት መካከል በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንዳስቻላትም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያም ከአስር ዓመታት በፊት በ30 የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች እንደተጀመረና አሁን ላይ ወደ 750 ተቋማት ማደጉን ገልጸዋል።

የካይዘን አሰራር ተግባራዊ ካደረጉ ኩባንያዎች መካከል 1ነጥብ7 በመቶ ያህሉ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኩባንያዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የካይዘን አመራር ሳይንሳዊ አሰራርን ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት በየዓመቱ 2 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር ከወጪና ከብክነት ለማዳን እንዳስቻላቸው አስታውቀዋል።

ከዚህ በላይ ማስፋትና ውጤታማ ማድረግ ይቻላል ያሉት አቶ መኮንን፤ በኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት የበጀትና የሰው ሃይል እጥረት በመኖሩና ለካይዘን ፍልስፍና ያለው ግንዛቤ ገና ዝቅተኛ በመሆኑ ብዙ ጉዞ ይቀራልም  ነው ያሉት።

በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የካይዘን አሰራር ባህል እንዲያሳድጉ ለማነሳሳት የአምስት ዓመታት ስትራቴክ እቅድ መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የካይዘን ኢንስቲትዩት  ፍልስፍና አማካሪ አቶ ወልደምህረት አረጋይ ናቸው።

በኮንፈረንሱ ከተሳተፉ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች መካከል የኩኋ ጋርመንት ኩባንያ የካይዘን ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዳኒኤል ገዛኢ እንዳሉት፣የካይዘን ምንነትና ውጤት የተገነዘበ ሰራተኛ ለማፍራት በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል።

ቀደም ሲል በተቋማቸው ውስጥ ሰዓታት ይወስድ የነበረ የጨርቃጨርቅ ምርት ዛሬ ላይ በደቂቃዎች ውስጥ በብዛትና በጥራት ማምረት መቻሉንም ተናግረዋል ።

በአጠቃላይ የካይዘን ፍልስፍና አሰራር 72 በመቶ የሚሆን ስራቸው ጥራት እንዲኖረውና ውጤታማ እንዲሆን አስችሎናል በማለት፤  ድርጅታቸው በፊት በዓመት ያገኝ  የነበረውን ከ100 ሚሊዮን ብር ገቢ ወደ 190 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን በማሳያነት  ጠቅሰዋል።

የፋብሪካው ስራተኛ ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በመምጣቱ በአሁኑ ሰዓት እያንዳንዱ ሰራተኛ ወርሃዊ ደሞዝ ከ1ሺ400 ብር በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የካይዘን ዘርፍ ባለሙያ አቶ አብረሃ ሃይሉ በበኩላቸው ከሶስት ዓመታት በፊት የፍልስፍናውን አሰራር ለመለማመድ ይቸገሩ እንደነበር ገልፀው፤ አሁን ግን የፋብሪካው ሰራተኞች በተሰማሩበት ሙያ ሁሉ በካይዘን የልማት ቡድን ተደራጅተው መስራት በመጀመራቸው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸው ተናግረዋል።