ለትምህርታችን ብቻ ትኩረት እንሰጣለን- በዲላ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች

123
ዲላ ጥቅምት 6 / 2012  ትምህርታቸውን ላይ ብቻ በማተኮር የመማር ማስተማር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለፁ። ዩኒቨርሲቲው   ለተመደቡለት  አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል እያደረገ ነው ። በዩኒቨርሲቲው ከተመደቡ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኤልሻዳይ ሄዴሳ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት ወደ ዩኒቨርሲቲው ስትመጣ በተደረገላት አቀባበል ተደስታለች። በቆይታዋ ለትምህርቷ ብቻ ትኩረት በመስጠት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን  የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻች። ተማሪ እስከዳር በለማ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ነባር ተማሪዎች  ከአውቶቡስ ስትወርድ ጀምሮ ባደረጉላት አቀባበል መደሰቷን ተናግራለች ። ተማሪዎቹ ባደረጉላት አቀባበል በቀላሉ አገልግሎቶችን ማግኘቷን የገለፀችው ተማሪ እስከዳር  ለትምህርቷ ትኩረት በመስጠት ዓላማዋን ለማሳካት እንደምትተጋ ገልጻለች ። የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ተክለጻዲቅ ደርበው እንዳለው ደግሞ የህብረቱ አባላት ከነዋሪዎችና  ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል። በትምህርት ጅማሮ ላይ የታየው መደጋገፍና ህብረት ለሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን አመላክቷል። የዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ፕሬዚዳንት ተማሪ ሀብታሙ ሞገስ በበኩሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ቀደም ብሎ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል። ተማሪዎቹ ከአውቶቡስ ሲወርዱ ጀምሮ መኝታ ቤታቸው እስከማድረስ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተናግሯል። "በዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት በተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዲስተካከሉ ተደርጓል" ብሏል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሃየሶ እንደገለፁት አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ እንዳይቸገሩ 200 ነባር ተማሪዎች ተመድበው አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል ። በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሰረት ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ዶክተር ዳዊት ገልፀው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም