በምስራቅ ጎጃም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ55ሺህ በላይ ህጻናት መደበኛ ትምህርት ጀመሩ

147

ጥቅምት 6 /2012 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው ዓመት ዘመን እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ55ሺህ በላይ ህጻናት ተመዝግበው መደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ መደረጉን የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጹ።

የመምሪያው  ምክትል ኃላፊ አቶ ዜና ማርቆስ ለኢዜአ እንደተናገሩት በየደረጃው ያለው አመራር እና የትምህርት ልማት ቡድኑ ባደረጉት ቤት ለቤት ምዝገባ እና ቅስቀሳ ትምህርት የጀመሩት ሰባት ዓመት የሞላቸው  ህጻናት ናቸው።

ከመስከረም 30/2012 ዓ.ም በኋላ ምዝገባ በማቆም ወደ መማር ማስተማር ስራው በማዞር የተመዘገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል እውቀትና ክህሎታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።

ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በመደበኛነት የአንደኛ ክፍል ትምህርት የጀመሩት ህጻናት ብዛት 55ሺህ 726 እንደሆኑ ተመልክቷል።

ይህም በዘመኑ 80ሺህ ያህል ህጸናትን ትምህርት ቤት ለማስገባት በእቅድ ከተያዘው ውስጥ ነው።

ለትምህርት ጥራት መጓደል  እንደ ምክንያት የሚነሳው ዘግይቶ ወደ ትምህርት ቤት መግባት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዜና ይህን ችግር ለማቃለል ምዝገባው መስከረም 30 ብቻ እንዲሆን ቀደም ብሎ በተካሄደው የትምህርት ንቅናቄ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት የእቅዱን ያህል ተማሪዎች መቀበል አልተቻለም።

ከተማሪ ወላጆች መካከል በጎዛምን ወረዳ የማይ አንገታም ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሉሰው ያየህ በሰጡት አስተያየተ ” ልጄ መማር በሚገባት እድሜ እንድትማር ወደ ትምህርት ቤት መላክ ችያለሁ” ብለዋል።

ከዚህ በፊት ሁለት ልጆቻቸውን ማስተማር ቢሞክሩም እድሜያቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ከህጻናት ጋር አብረን አንማርም በማለት አቋርጠው ወደ ግብርናው ስራ መሰማራታቸውን አስታውሰዋል።

እርሳቸውም በጎልማሶች ትምህርት ተምረው ማንበብ እና መጻፍ ቢፈልጉም ያልተሳካላቸውን አሁን በልጃቸው ለመካስ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

“ልጆቼን አለማስተማሬ ስለቆጨኝ በዚህ ዓመት ሁለት የልጅ ልጆቼን ከቤተሰቦቻቸው በማምጣት እንዲማሩ አስመዝግቤያለሁ ” ያሉት ደግሞ በማቻከል ወረዳ የላሎማ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ነጠሩ መኩሪያው ናቸው።

በአነደድ ወረዳ የወቢ እነችፎ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ እመናት አጉማስ በበኩሏ ዘንድሩ መማር በመጀመሯ መደሰቷን ገልጻ አምና የእድሜ እኩዮቿ መማር በመጀመራቸው ማንበብ እና መጻፍ መቻላቸውን አይታ ቆጭቷት እንደነበር አስታውሳለች።

በተያዘው የትምህርት ዘመን በምስራቅ ጎጃም በቅድመ መደበኛ፣ መጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ697ሺህ በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ እንደሚገኙ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።