በአፋር ክልል ጥቃቱን በማውገዝ ሰልፍ ተካሔደ

247

ሰመራ፤ ኢዜአ፤ ጥቅምት 6/2012 በአፋር ክልል በህፃናትና በሴቶች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሔደ።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አህመድ ከሎይታ እንደተናገሩት ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት በአፋምቦ ወረዳ በንጹሃን ሰዎች በተለይም ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በተፈፀመው ጥቃት 18 ሰዎቸ ሲሞቱ 36 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውሰዋል ።

ጥቃቱን ተከትሎ ትናንት በአዋሽ፣ ገዋኔ፣ ቡሪሙዳይቶና አፋምቦ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፉ ተካሄዷል።

ሰልፈኞቹ በህዝቡ ላይ የሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችና የግፍ ግድዎች በአስቸኳይ መንግስት እንዲያስቆምላቸውና ወንጀለኞችን ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል ።

የተቃውሞ ሰልፉ ዛሬም በሎግያ፣ በራህሌ ፣ አበአላ ፣ መጋሌና ኢረብቲ ወረዳዎች ተካሂዷል ።

በነገው እለትም የተቃውሞ ሰልፉ በተለያዩ ወረዳዎች እንደሚቀጥል ኃላፊው ተናግረዋል ።

በበራህሌ ወረዳ ዛሬ በተካሔደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈው ወጣት ኡስማን ናስር በሰጠው አስተያየት በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችን ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ ለመጠየቅ በራሳችን ተነሳሽነት የተዘጋጀ ሰልፍ ነው ብሏል ።