በጎንደርና አካባቢው የተከሰተውን ሁከት ለማስቆም ውሳኔ ተላለፈ

102
ጥቅምት 6/2012 በማዕከላዊ፣ በምዕራብ ጎንደር ዞኖችና በጎንደር ከተማ በየጊዜው የሚከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ርምጃ ለመውሰድ ውሳኔ ማሳለፉን የአማራ ክልል ደህንነትና የጸጥታ ካውንስል አስታወቀ። በቅማንት የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የቀረበው ጥያቄ በህገ-መነግስቱ ቢመለስም አካባቢውን ላለፉት ዓመታት የሁከትና ብጥብጥ ቀጠና በማድረግ በቅማንትም ሆነ በአማራ ማህበረሰቦች ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን መግለጫ አውስቷል። ጥያቄው ተገቢው ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ ቢደረግም እየታየ ያለው ጸረ ህገ-መንግስታዊ እንቅስቃሴ የህዝቡን በሰላም የመኖር መብት የተጋፋ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። የኮሚቴው ህገ-ወጥ እቅንቅስቃሴ ለአካባቢው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት መሆኑን መግለጫው ጠቁሞ በተለይም ከመስከረም 15/2012 ዓ.ም ጀምሮ በተከሰተው ግጭት የአገሪቱ የወጭ ንግድ ማስተናገጃ የሆነው የጎንደር መተማ መስመር ላይ ችግር አስከትሏል። የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስታት በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት ችግሩ በሰላማዊና ህግን በተከተለ ሁኔታ ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ወደ ውጤት ሊቀየር አለመቻሉን መግለጫው አውስቷል። የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስታት በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት ችግሩ በሰላማዊና ህግን በተከተለ ሁኔታ ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ወደ ውጤት ሊቀየር አለመቻሉን መግለጫው አውስቷል። በመሆኑም የፌደራል መንግስት ጣልቃ በመግባት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያስተካክል የክልሉ መንግስት ጥሪ ማቅረቡን በመግለጫው ተመልክቷል። የኢፌዴሪ መከላከያ ሃይልን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላት ማንኛውንም ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላምና መረጋጋት እንዲያሸጋገሩ መመሪያ መተላለፉን መግለጫው አመልክቷል። በዚህ መግለጫ መሰረትም አካባቢውን በማወክ ተግባር ላይ የተሰማራ ማንኛውንም አካል ለመቆጣጠር አስፈላጊውን የሃይል አማራጭ በመጠቀም ለህግ በማቅረብ ወደ ግጭቱ የገቡ ሃይሎች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለሱ ይደረጋል። ማንኛውም አካል ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለበትና ይሔንን በሚያደናቅፍ ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ያመለከተው መግለጫው በታወቁ የፀጥታ ኃይሎች ከተያዙት ትጥቅና መሳሪያ ውጪ በአካባቢው ላልተወሰነ ጊዜ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለና የሚወረስ መሆኑን አስታውቋል። የቅማንት አስተዳደር ቀደም ሲል በተወሰነው ህጋዊ ውሳኔ መሰረት በህዝብ ይሁንታ የሚደራጅ የራስ አስተዳደር በማቋቋም አገልግሎት እንዲጀምር የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ አካል ተቀባይነት የሌለው ሲሆን በተለያየ ምክንያት በግጭቱ ተሳትፎ የነበረው ኃይል እስከ ጥቅምት 20/2012 ዓም ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ጥሪ መቅረቡንም አመልክቷል። በግድያ የተሳተፉ ግለሰቦች ጉዳይ በህግ መታየቱ እንዳለ ሆኖ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴዎችን በየደረጃው ያለው አመራር፣ ነዋሪና ዜጋ የመቆጣጠር፣ የማሳወቅ፣ እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ይህ ካልሆነ ከተጠያቂነት ባለፈ በአካባቢው የሚገኘው ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተራግፎ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል። ህግን በማስከበር ሰበብ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት የሚደረግ እንቅስቃሴን የከለከለው መግለጫው ከጎንደር-መተማ ፣ ከጎንደር-ሁመራ፣ ከጎንደር-ባሕር ዳር፣ ከጎንደር-ደባርቅ የሚወስዱ መንገዶች እንዲሁም በጎንደር ከተማና ዙሪያው ነጻ ሆነው እንቅስቃሴዎችን የማደናቀፉ ኃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አመልክቷል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል የፀጥታ ኃይል፣ በየደረጃው ያለው የክልሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በቅንጅትና በጥምረት ለተሟላ ሰላም እንደሚሰሩ በመግለጫው ያመለከተው የክልሉ ደህንነትና የጸጥታ ካውንስል ሁሉም የሰላም ኃይሎች የተሟላ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም