የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌከትሮኒክስ ቪዛ 200 ሺህ መንገደኞችን አስተናገደ

140

ጥቅምት 6/2012 በአገሪቱ እ.አ.አ በ2017 የተዋወቀውን የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎት ተከትሎ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መንገድ በሯን ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት አድርጋለች።

አገልግሎቱ ይፋ ከተደረገበት እለት አንስቶ ጎብኚዎች ከየትኛውም የአለም ክፍል ሆነው በአገልግሎቱ በመጠቀም በቀላሉ ወደ አገሪቱ መግባት ችለዋል።

ይህን ተከትሎ ከ217 አገሮች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ 200 ሺህ ጎብኚዎች አገሪቱን ረግጠዋል።

መንገደኞቹ አገልግሎቱን ከ 6፡00 ሰአት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማግኘት ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ያለመጉላላት መስተናገድ መቻላቸውን አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

“ የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎቱን በመጠቀም አገሪቱን የሚጎበኙ ተጓዥች ቁጥር እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በቱሪዝምና በጉዞ ኢንዱስትሪ ውስጥ ላለነው በጠቅላላ መልካም ዜና ነው” በማለት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ተናግረዋል።

“የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ በመጠቀም ወደ አገሪቱ የገቡት ጎብኚዎች ቁጥር 200 ሺህ መድረሱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ያሳየናል። ይህም ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ሲሆን በጉዞ፣ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት አገሪቱንም ተጠቃሚ ያደርጋታል” ሲሉ ገልጸዋል።

አለም አቀፍ ጉባኤዎች፣ ማበረታቻዎችና የኮንፈረንስና አውደ ርዕይ ዝግጅቶች መስፋፋት ከኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎቱ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ፍሬ እንድታገኝም አግዟታል።

የአየር መንገዱ የበረራ ትስስር በማደግ ላይ ካለው የሆቴል አገልግሎት እና ከላይ ከተጠቀሱት አማራጮች ጋር ተዳምሮ አገሪቱን ተመራጭ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መናኸሪያ እንደሚያደርጋት ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የጉዞ ክንውኖችን ቀላልና ቀልጣፋ በማድረግ በኩል ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቷ ተጠቃሚነቷ እየጨመረ መጥቷል።

ከኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎቱ በተጨማሪ መንገደኞች የሞባይል መተግበሪያዎችን በመጠቀም የአየር መንገዱን አገልግሎት ማግኘታቸው እድገቱን እንዳፋጠነው አየር መንገዱ የላከልን መግለጫ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም