ኢትዮጵያ የእንግሊዝ የግንባታ አማካሪዎች የገበያ አማራጭ ልትሆን እንደምትችል ተገለጸ

50
ጥቅምት 6/2012 ኢትዮጵያ፣ ማሌዥያና ሜክሲኮ ለእንግሊዛውያን አማካሪዎች ቀዳሚ ከሆኑት 10 የግንባታ ዘርፍ አማራጮች ውስጥ መካተታቸውን መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው የአማካሪዎችና ኢንጅነሮች ማህበር አስታወቀ። በአለም አቀፍ ደረጃ በግንባታ ዘርፉ ገበያ ውስጥ 23 በመቶ ድርሻ የያዘችው ቻይና በዝርዝሩ አልተካተተችም። ተቋሙ ያስቀመጠውን የገበያ ስፋት፣ የእድገት አቅም፣ ሙስናን መዋጋት፣ የህግ የበላይነትና ግልጽነት የሚሉትን መስፈርቶች ቻይና እንደማታሟላ አሶሲየሽን ኦፍ ኮንሰልታኒሲ ኤንድ ኢንጅነሪንግ (ACE) ወይም የአማካሪዎችና ኢንጅነሮች ማህበር ጠቅሷል። “ኢትዮጵያ በእኛ ዝርዝር ውስጥ በመካተቷ ሁሉንም የምታነጋግር አገር ሆናለች”በማለት አለም አቀፉን የግንባታ ዘርፍ በተመለከተ ትንበያ የሚሰጠው የግሎባል ኮንስትራክሽን ፐርስፔክቲቭ ዳይሬክተር ግራሃም ሮቢንሰን ተናግረዋል። ከኦክስፎርድ ኢኮኖሚክስ ጋር በመሆን ለአማካሪዎችና ኢንጅነሮች ማህበር ጥናቱን ያከናወኑት ግራሃም “ገንዘብን መከተል ቀላል ጉዳይ ነው” በማለት ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ድንበር ዘለል ድጋፍና የአለም ባንክ የተለያዩ ድጋፎች ዋነኛ ተጠቃሚ መሆኗን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ጥራት ከ141 አገሮች 123ኛ ላይ መቀመጧን ጠቅሰው ፈጣን አድገት፣ ለስራ የደረሰ ወጣት ጉልበት በአሁንና እ.አ.አ በ2030 በዘርፉ ከፍ ያለ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የከተሞችን ማስተር ፕላን በማሻሻል ግንባታ ይከናወንባታል በማለት ትንበያቸውን አስቀምጠዋል። በገበያ ስፋት አሜሪካ፣ ህንድና ኢንዶኔዥያ ቀዳሚ ኢላማ መሆናቸውና ለግንባታው ዘርፍ ወጪ በማድረግ እ.አ.አ ከ 2018 እስከ 2030 በቅደም ተከተል 22 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ፣ 10 ትሪሊዮንና 6 ትሪሊዮን ዶላር ያፈሳሉ ተብሎ ተገምቷል። ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ሳዑዲ አረቢያም ከ10ሩ አገሮች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። የአማካሪዎችና ኢንጅነሮች ማህበሩ አለም አቀፍ ኤክስፖርት ሰትራቴጂ ለህትመት የበቃው ከትናንት በስቲያ ሲሆን ቀጣዩን የአማካሪዎች መዳረሻ ከአቅርቦት ሰንሰለቱ ጋር በማስተሳሰር የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም