የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰራሩን ለማዘመን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ገለጸ

74
አዲስ አበባ ጥቅምት 5 /2012  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተያዘው በጀት ዓመት የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን ለማዘመን የሚረዳ የህንጻ ግንባታ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ። ከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የስማርት ሜትር ቴክኖሎጂ እንዲያገኙ የሚያስችል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጿል። እንዲሁም በደንበኞችን ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ ምቹና አዋጭ የክፍያ ስርዓቶች በጥናት መለየቱን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ፣ የትራንስፎርመሮች ተከላና የመልሶ ግንባታ ስራዎች በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው። ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶችን በጥናት በመለየት የተሻለ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ማቀዱን ገልጸዋል። ከኤሌክትሪክ ጋር በተያያዘ በሰው አካልና ህይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋና ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ስራ እንደሚከናወንም አቶ መላኩ አመልክተዋል። የኤሌክትሪክ ሽፋን ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መካከለኛና ዝቅተኛ የኤሌትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።                                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም