የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሰላም ኖቤል ሽልማት ደስታውን ገለጸ

143

ጋምቤላ ጥቅምት 5 / 2012 የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ጠቅላይ ሚነስትር ዓቢይ አህመድ ባከናወኗቸው የሰላምና የአንድነት ሥራዎች የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ በመሆናቸው ደስታውን ገለጸ፡፡
ድርጅቱ አገራዊውን ለውጥና አንድነት ለማስቀጠልና የክልሉን ሰላም በመጠበቅ ሚናውን እጫወታለሁ ብሏል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ፒተር ኡማን ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአካባቢው አገሮች በሰሯቸው የሰላምና የአንድነት ስራዎች የኖቤል ሰላም ተሸላሚ በመሆናቸው ድርጅቱ ደስታ ተሰምቶታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በተለይም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የነበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሰላም ወደ አገር ቤት ገብተው ለአገሪቱ ሰላም፣ልማትና አንድነት የሰሩ መሪ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ከ20 ዓመታት በላይ የተለያዩትን የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች  ለማቀራረብ ያደረጉት ጥረት መላው ዓለምን ያስደመመ ተግባር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል የነበሩ አለመግባባቶችን በመፍታት አካባቢው የልማትና የሰላም ቀጠና ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት አበረታች መሆኑን ሊቀመንበሩ  ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረውን የልማትና አንድነት ጉዞ ለማስቀጠል ከክልሉ ሕዝብ ጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡