በአፋር ክልል የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ

106
ሰመራ ጥቅምት 5 / 2012  በአፋር ክልል ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች በስምንት ወረዳዎች ተካሄዱ። የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የነበረውን ጥቃት በማውገዝ ሰልፎቹ ትናንትና ዛሬ  በወረዳዎቹ ተደርገዋል። ሰልፎቹ ትናንት  በአዋሽ፣ በገዋኔና ቡሪሙዳይቶና አፋምቦ ወረዳዎች ነበር። ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች በበራህሌ፣ አብአላ፣ በመጋሌና ኢረብቲ ወረዳዎች ዛሬ ተካሂደዋል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በዚሁ ወቅት ''የሽብር ጥቃቶችና የግፍ ግድያዎች በአስቸኳይ መንግሥት ያስቁምልን!'' ፣ ''ወንጀለኞች ለሕግ ይቅረቡ!''  የሚሉ መፈክሮችን በዋነኛነት ይዘው ነበር። ባለፈው ቅዳሜ ለሊት በአፋምቦ ወረዳ የንጹሃን ሰዎች በተለይም ህጻናትና ሴቶች ላይ በተፈጸመው ጥቃት 18 ሰዎች ሲሞቱ ፣36 ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱ አካባቢዉን የግጭት ቀጠና በማድረግ በኮንትሮባንድና ተያያዥ እንቅስቃሴ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚፈልጉ ኃይሎች እንደተሳተፉበት የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ግምቱን አስቀምጧል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም