ለትምህርታችን ትኩረት በመስጠት ሰላማዊ የመማር ማስተር ሂደት እንዲኖር ኃላፊነታችንን እንወጣለን- አዲስ የተመደቡ ተማሪዎች

64
ድሬዳዋ/ሐረር/ጭሮ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ለትምህርታችን ትኩረት በመስጠት ለመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊነት ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በድሬዳዋ ፣ ሐሮማያና ኦዳቡልቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ለተመደቡላቸው ከ9 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች አቀባበል እያደረጉ ነው ። ተማሪዎቹ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል ። በዩኒቨርሲቲዎቹ የተመደቡ አዲስ ተማሪዎች አቀባበል እየተደረገላቸው ያለው በዩኒቨርሲቲዎቹና በከተሞቹ አስተዳደር አመራሮች፣ በነባር ተማሪዎችና ነዋሪዎች ነው። በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ አዲስ ተማሪዎች መካከል ተማሪ አብዱራዛቅ አልዪ “የህዝቡ ፍቅር ይማርካል። ነባር ተማሪዎችም ያለምንም ችግር ወደ መኝታ ቤታችን አስገብተውናል በተደረገልን አቀባበል ተደስተናል” ብሏል፡፡ ከጎንደር የመጣው ተማሪ ዮሴፍ ይግዛው በበኩሉ “ስለድሬዳዋ የሰማሁትን ፍቅርና መተባበር በተደረገልን አቀባበል በማየቴ ተደስቻለሁ” ሲል ተናግሯል። የተማሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ከማክበር ጀምሮ ለሰላም ዋጋ እንደምትሰጥ የገለፀችው ደግሞ ተማሪ ራሄል ዓለሙ ናት፡፡ “አዲስ ገቢ ተማሪዎች ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ድጋፍ እያደረግንላቸው ነው” ያለው ነባር ተማሪ ንጉሴ መላኩ በበኩሉ አዲስ ተመዳቢ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲው በተመደቡ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ ከባቡር ጣቢያና ከመናኸሪ እያተቀበሉ መሆኑን ተናግሯል ። የከተማው አገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ጨርሰው እስኪወጡ ድረስ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል ። የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ዩኒቨርሲቲው ለ14ኛ ጊዜ 4ሺህ 94 አዲስ ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ-ካርታ መሠረት ትምህርታቸውን እንደሚጀምሩገልጸው፣ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጠናከር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል ። እንደ ዶክተር ኡባህ ገለፃ አምና በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀውን የተማሪዎች የሥነ-ምግባር ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል ። ከነገ ጀምሮ ከተማሪዎችና መምህራን ጋር በደንቡ ላይ ውይይት ይደረጋል ። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ዩኒቨርሲቲው ተልዕኮውን በተሳካ መንገድ ዳር እንዲያደርስና ተማሪዎች የመጡበትን መሠረታዊ ዓላማ እንዲያሳኩ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዳዲስ ተማሪዎችም በተደረገላቸው አቀባበል መደሰታቸውን በመግለፅ፣ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ። ከእንጅባራ የመጣው ተማሪ ቸርነት ካሳሁን ነዋሪዎች የአካባቢውን ባህል በሚገልፅ አለባበስና ጭፈራ ባደረጉላቸው አቀባበል መደሰቱን ገልጿል። “ወጣቶችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የያዝኳቸውን ዕቃዎች ከማጓጓዝ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገውልኛል” ብሏል ። “ከፖለቲካና ከአጓጉል ተግባራት ነፃ በመሆን ትምህርቴ ላይ ብቻ በማተኮር ለመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊነት ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ” ሲልም  ተናግሯል ። አቀባበሉ ከጠበቀው በላይ እንደሆነበት የተናገረው ደግሞ ከባቱ የመጣው ተማሪ ክብርዓብ በላይ ነው። “የተደረገልኝ አቀባበልም ጠንክሬ ለመማርና ስኬታማ ለመሆን መነሳሳት ፈጥሮብኛል” ብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ከሌሎች ተማሪዎችና ከአካባቢው ማህበረሰብ በመተባበር ድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል። ልጃቸውን ከሐዋሳ ይዘው የመጡት ወይዘሮ ንግስት ጀማ በበኩላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ለአዳዲስ ተማሪዎች ባደረገው አቀባበል መደሰታቸውን ገልጸዋል ። “ነባር ተማሪዎችና ወጣቶች ባደረጉን አገዛ ከእንግልትና መጉላላት ታድጎናል” ብለዋል ። ተማሪዎች ተቻችለው፣ አንድነታቸውን አጠናክረውና ተረዳድተው የመጡበትን ዓላማ ማሳካት ይገባቸዋል” ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል መላዕከ ስብሃት ውለታው ከሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ወጣቶችና እናቶች ጋር በመሆን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች አቀባበል እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። “ተማሪዎችን ቤተሰባዊ በሆነ ፍቅር እየተቀበልን እንገኛለን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሀቢባ አብዱልሰላም ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዚህ የትምህርት ዘመን 4ሺህ 200 አዲስ ተማሪዎች እንደተመደቡለት ታውቋል ። በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡ አዲስ ተማሪዎች መካከል ወጣት ወንድም አገኝ በልሁ በነዋሪዎችና ነባር ተማሪዎች በተደረገለት አቀባበል መደሰቱን ተናግሯል። በቆይታው ከፖለቲካና ከአጓጉል ተግባራት በመራቅና ትምህርቱ ላይ ብቻ በማተኮር የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት መዘጋጀቱን አስታውቋል። ልጆቻቸውን ይዘው ከመጡ ወላጆች መካከል አቶ ሰይፉ ከበረ በሰጡትአስተያየት የአካባቢው ማህበረሰብና ነባር ተማሪዎች ለአዲስ ተማሪዎች ያደረጉላቸው አቀባበል ያለስጋት እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ለ1ሺህ 400 ተማሪዎች አቀባበል እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም