የሐሸንገ ሃይቅን ከጥፋት ለመታደግ 15 ሚሊዮን ብር ተመደበ

60
ጥቅምት 04/12 ማይጨው ኢዜአ .... የሐሸንጌ ሐይቅን ከመጥፋት አደጋ በመታደግ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ የተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦፍላ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ። የኦፍላ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቱ ኪዳነ እንደገለፁት በሐሸንገ ሐይቅ ዙሪያ በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች በማከናወን ሃይቁን ከጥፋት ለመታደግ ርብርብ እየተደረገ ነው ። የአካባቢ ጥበቃ ስራው ሃይቁ ለተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲውል የሚያመቻች ጭምር መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው አባባል ከሆነ የሐሸንገ ሃይቅ ትኩረትና እንክብካቤ ሳይደረግለት በመቆየቱ ምክንያት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል። በአካባቢው ላይ የነበረው የተፈጥሮ ደን እየጠፋ በመምጣቱና  በዙሪያው ከሚገኙ ሰንሰላታማ ተራሮች ወደ ሐይቁ የሚገባው ከፍተኛ የጎርፍ ደለል መጠኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀንስ እንዳደረገው ገለፀዋል ። በአደጋው በሃይቁ ውስጥ በሚገኙ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች ላይ ጭምር ጉዳት ሲደርስባቸው እንደቆየም ነው ኃላፊው የተናገሩት። በደለሉ ምክንያት የሀይቁ ጥልቀት ከ25 ሜትር ወደ 14 ሜትር ዘቅ አድርጎታል ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በ2011 ዓ.ም ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መስሪያ የሚውል ሰባት ሚሊዮን ብር ተመድቦለት ተስፋ ሰጪ ስራዎች ማከናወን ተችሏል ። በቀጣይነትም ሐይቁ ሙሉ በሙሉ ከመጥፋት ስጋት እንዲላቀቅና የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማልማት አንዲቻል የክልሉ መንግሰት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ኃላፊው ተናግረዋል ። በኦፍላ ወረዳ የመንከረ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ቄስ መሪ ሸኮለ እንደተናገሩት  የሐሸንጌ ሐይቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ በደለል እየተሞላ መጠኑ እየቀነሰ መጥቶ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ነበር ብለዋል። የሃይቁ የውሃው መጠን እንዲቀንሰ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በአካባቢው የነበረው የደን መመናመን መሆኑን ገልፀው የአካባቢ ጥበቃ ስራ በማከናወን ልንታደገው  እየተረባረብን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል ። በሃይቁ ዙሪያ የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በሁሉም ተፋሰሶች ላይ ቀጣይነት ቢኖረው ሐይቁ ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ እንደሚሆን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ  አርሶ አደር ባዬ ዘገየ ናቸው። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወነው ስራ  ውጤትማ በመሆኑ ተስፋቸው መለምለሙን የተናገሩት አቶ ባዬ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልፀዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም