የደቡብ ክልል ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ

98

ሀዋሳ፤ ኢዜአ ጥቅምት 04/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሰጣቸውን ሽልማት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽልማት መሆኑን መግለፃቸው የሠላም ዋጋ እጅግ የከበደና ባለቤትነቱም የእያንዳንዱ ግለሰብ መሆኑን እንደሚያሳይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ገለፁ።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጀመረ  ፡፡

የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ጉባኤው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የ2019 የአለም የሠላም ኖቤል ተሸላሚ በሆኑበት ወቅት መካሔዱ ልዩ ያደርገዋል ካሉ በኋላ በምክር ቤቱ ስም የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን መግለፃቸው የሠላም ዋጋ እጅግ የከበደና ባለቤትነቱም የእያንዳንዱ ግለሰብ መሆኑን እንደሚያሳይ ወይዘሮ ሄለን ገልፀዋል ።

በተለይም የምክር ቤት አባላት ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ ከመሪያችን ጎን በመሰለፍ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል ፡፡

በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የተለያዩ ፈተናዎች የገጠሙት ቢሆንም በርካታ አበረታች ውጤቶችና አዳዲስ ተስፋዎችን የፈጠረ እንደሆነ ገልፀው መንግስት በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ላይ ያሳየው ቁርጠኝነት ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና አፈ ጉባኤዋ ገለፃ በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ በደቡብ ክልልም በርካታ ችግሮች ተስተናግደዋል ፡፡

ነገር ግን የክልሉ ህዝቦች በአስተዋይነትና በኃላፊነት መንፈስ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ለመፍታትና የመፍትሔው አካል ለመሆን ያሳዩት ተነሳሽነት ተገቢና ወቅቱን የሚመጥን ነው ብለዋል ፡፡

አሁን በክልሉ አንፃራዊ ሠላም መስፈኑን የተናገሩት ዋና አፈ ጉባኤዋ ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ህብረተሰቡን በፍጥነት ከነበረበት ሥነ-ልቦና ማላቀቅና ወደ ቀድሞው መደበኛ የዕለት ተእለት እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል ፡፡

ዛሬ የተጀመረው ጉባኤው ለተከታታይ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የ2011ዓም  ክንውንና የ2012 ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ፤ ልዩ ልዩ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም የተለያዩ ሹመቶች እንደሚፀድቁ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም