ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከፊንላንዱ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒሲቶ ጋር ተወያዩ

86
ጥቅምት 4/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፊንላንዱ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒሲቶ ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያዩ። ሁለቱ መሪዎች የጋራ ጥቅምን እውን በሚያደርግ መልኩ የአፍሪካና የአውሮፓን ግንኙነት በማጠናከር ሂደት ላይ መክረዋል። ፕሬዚዳንት ሳውሊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያገኙት የሰላም የኖቤል ሽልማት 10 በመቶ እውቅና፣ 90 በመቶ ደግሞ ለሰላም በርትተው እንዲሠሩ የተሰጣቸው አደራ እንደሆነ ተናግረዋል። ለውጡ ያስገኛቸውን ዋና ዋና ስኬቶች በመግለፅ የፊንላንድ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግባቸው የሚችልባቸውን የልማት አቅጣጫዎችም ጠቁመዋል። የፊንላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ስራዎች ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ሁለቱ አገሮች 60 ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም አላቸው። የ71 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒሲቶ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል። የሶሊ ኒኒስቶ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል በፕሬዚዳንት ደረጃ የሚካሄድ የመጀመሪያ ጉብኝት ነው። ጉብኝቱ ፕሬዚዳንቱ እ.አ.አ 2012 ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአፍሪካ አገር የሚያደርጉት የመጀመሪያው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም