የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴው ለካርድ ማተም የሚወጣውን 35 ሚሊዮን ብር ያስቀራል

76
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 4 ቀን 2012 በተያዘው በጀት ዓመት 15 በመቶ የሞባይል አየር ሰዓት አገልግሎት በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ የሚሰጥ መሆኑን ኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ። የኢትዮ-ቴሌኮም የሽያጭ ክፍል ዋና ኦፊሰር አቶ መሃመድ ሀጂ ለኢዜአ እንዳሉት በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚወጣበት የሞባይል ካርድ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል። እስካሁን ከ7 እስከ 8 በመቶ የአየር ሰዓት ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ያሉት አቶ መሃመድ፤ በ2012 በጀት ዓመት ግን 15 በመቶ ክፍያውን በዚሁ ዘዴ ለመፈጸም እንደታቀደ ተናግረዋል። ይህ የክፍያ ዘዴ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት። ''የይሙሉ'' አገልግሎትን በአከፋፋዮችና በቸርቻሪዎች አማካኝነት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረጉን የገለጹት አቶ መሃመድ፤ በተያዘው ዓመትም ኢ.ቪ.ዲ (ኤሌክትሮኒክስ ቮይቸር ዲስትሪቢዩሽን) በተባለ ዘዴ የፖስ ማሽኖችን በመጠቀም አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። የኤሌክትሮኒክስ አየር ሰዓት መሙያ ዘዴው ለካርድ ማተም የሚወጣውን  35 ሚሊዮን ብር ወጪንም የሚያስቀር መሆኑን ነው የገለጹት። ዘዴው የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈ ለአገሪቷ የዲጂታላይዜሽን ዕድገትና ለአካባቢ ጥበቃም የጎላ ሚና እንዳለውም ይናገራሉ። ''ኢትዮ-ቴሌኮም ከውጭ የሚገባውን ካርድ ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይችልም ወደ 20 በመቶ ለመቀነስ ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ ነው'' ያሉት ኦፊሰሩ፤ በዚህ ዓመትም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያው15 በመቶ እንደሚደርስ ያነሳሉ። ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር ሌሎች አጋር ድርጅቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ መሃመድ፤ ለአብነትም ባንኮች በሞባይል ዋሌት አማካኝነት የሚሰጡትን አገልግሎት ጠቅሰዋል። 177 ሺ ጅምላ ሻጮችና ቸርቻሪዎችም በዚሁ ዘርፍ  ከተቋሙ ጋር እየሰሩ መሆኑን በማከል። የኤሌክትሮኒክስ የአየር መሙያ ዘዴው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚያስቀር መሆኑንም አቶ መሃመድ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም