የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ከ7ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየታደሰ ነው

70
ጅማ ጥቅምት 4 / 2012 የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ከ7ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየታደሰ መሆኑን የቤተ መንግሥቱ ተጠሪ ገለጹ። ተጠሪው አቶ ክብሩ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የቤተ መንግሥቱ ዕድሳት እየተከናወነ ያለው ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ ድጋፍና ከመንግሥት በተመደበ በጀት ነው። እድሳቱ ከተጀመረ ስድስት ሳምንታት ማስቆጠሩን አስረድተው፣ሥራውም ከአሜሪካና ከኢትዮጵያ በተውጣጡ ባለሙያዎች እየተከናወነ  መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እድሳቱን በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም አስረድተዋል። የቤተ መንግሥቱን ዕድሳት በማከናወን ላይ ከሚገኙ የቅርስ ዕድሳት ባለሙያ አቶ መሐመድ ሐሰን ጥራቱ በተረጋገጠ የቀረሮ፣የወይራ፣የጥቁር እንጨትና የአበሻ ጽድ እንጨት በመጠቀም እድሳቱን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በመታደስ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ እድሳቱ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቅ ግብዓቶችንና የሥራ መሣሪያዎች እንደሚሟሉላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ጀሃድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት የቤተ መንግሥቱ እድሳት በመጀመሩ መደሰታቸውን ይናገራሉ። ዕድሳቱ በፍጥነትና ጥራት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ቤተ መንግሥቱ የማንነታቸውን መገለጫ በመሆኑ በእርጅና ብዛት ለመፍረስ ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ሲያዝኑ እንደነበር ገልጸዋል። ከዕድሳት ስራው በተጨማሪም ከዋናው ከተማ እስከ ቤተ መንግሥቱ የተሰራው የጠጠር መንገድ ርክክብ እንዲፈጸም ጠይቀዋል፡፡ አባ ጅፋር በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጅማና አካባቢውን የገዙ መሪ ሲሆኑ፣መቀመጫቸውን ጅሬን በሚባል አካባቢ በማድረግ ቤተ መንግሥታቸውን መገንባታቸው ይታወቃል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም