ግድቡ ከሚያመነጨው ኃይልና ከሌሎች ዘርፎች የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ነው …ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት

697

ኢዜአ፤ ጥቅምት 4/2012 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሚያመነጨው ኃይል ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ  ከቱሪዝም ና ከሌሎች ዘርፎች የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ እንደሚሆን የግድቡ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ  አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቁሟል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ  ብሄራዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ አብረሃም  ለኢዜአ እንደተናገሩት ግድቡ ለሀገሪቱ ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ፕሮጀክት ነው፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የሃይል አቅርቦት ከማደጉ በተጨማሪ በየአመቱ ግድቡ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ አቶ ሃይሉ ተናግረዋል።

ገቢው በቀጣይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችና ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት አቅም እንደሚፈጥር የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ግድቡን በራስ አቅም መስራት መቻሏ ሌሎች ሀገራት በሀገሪቷ ላይ እምነት እንዲያሳድሩና  ብድርን በቀላሉ ማግኘት እንዲትችል እያደረገ ነው ብለዋል።

ግድቡ ኃይልን ከማመንጨት በተጨማሪ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ  እንዳለው የተናገሩት አቶ ሃይሉ፤ ካርቦንን በመሸጥ ሀገሪቱ ገቢ እንድታገኝም ያደርጋታል ነው ያሉት።

በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ በበኩላቸው ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት በተጨማሪ የዓሳ ልማትና ሌሎች ትላልቅ ልማቶች የሚካሄድበት ፕሮጀክት እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በግድቡ ሐይቅ የዓሳ ምርትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ከማስቻሉ በተጨማሪ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚያስችልም ነው አቶ ተፈራ የገለጹት።

በተለያዩ ሀገራት ትላልቅ ሐይቆች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ስለሚጎበኛቸው የገቢ ምንጭ እንደሚሆኑ የተናገሩት አቶ ተፈራ፤  ኢትዮጵያም  ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ከጎብኝዎች ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደምትችል ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት እስኪበቃ ድረስ ሁሉም ህብረተሰብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በቀጣይ አራት አመታት ውስጥ  ግንባታው ተጠናቆ  ለአገልግሎት እንደሚበቃ የተናገሩት አቶ ሃይሉ፤ በቀጣይ አመትም ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል።

ከስድስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታው 68 በመቶ መድረሱን ከጽ/ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል።