” በጥረት የተገኘ ተስፋ ሰጪ ውጤት “

2799

ዳዊት ደሳለኝ  (ኢዜአ )

ወይዘሮ አዳነች ቱሉ ይባላሉ። በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በግራር ጃርሶ ወረዳ በወርጡ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ናቸው። በአካባቢያቸው የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ መኖሩን ይመሰክራሉ። ወላዶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ መበረታታቱና በስርዓተ ምግብ ላይ ግንዛቤ ማደጉንም እንደዚሁ።

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት በርካታ ሕፃናት ለበሽታና ለአካል መቀጨጭ ይዳረጉ እንደነበር የገለፁት ወይዘሮ አዳነች በተመጣጠነ የምግብ አዘገጃጀት ላይ በተለያየ ጊዜ የተሰጠው ስልጠና በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን ጨምሮ የሌሎች ጐረቤቶቻቸው የአመጋገብ ልማድ መቀየሩን ገልፀዋል።

ወይዘሮ አዳነች ነፍሰ ጡር ሴቶችና ሕፃናት እንዴት መመገብ እንዳለባቸው በቂ እውቀት ከስልጠናው እንዳገኙ ይገልፃሉ። በተለይ በቡድን ተደራጅተው እህልና ገንዘብ በማዋጣት ወላዶች የተመጣጠነ ምግብ በቀላሉ እንዲያዘጋጁ እድል እንደሰጣቸውም ይናገራሉ።

ብዙ ትኩረት የማይሰጡትን የጓሮ አትክልት በቤት ውስጥ በዋና ምግብነት በማዘጋጅትም ጤናቸውን ለመጠበቅና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል እንዳስቻላቸው በተግባር አይተውታል፡፡

በዚህ ወረዳ በጫገል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ለ36 ዓመታት የኖሩት ወ/ሮ ፀሐይ ታደሰ በአቅራቢያቸው የጤና ተቋም መከፈቱና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ሕብረተሰቡን በኘሮግራምና በተለያዩ አጋጣሚዎች ማስተማራቸው በተለይ የእናቶችና ሕፃናት ሕይወትን ከከፋ ጉዳትና ሞት እንደታደገ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ቀደም ባሉት ዓመታት ነፍሰ ጡር እናቶች ክትባት አያገኙም። የሚወልዱትም ግንዛቤ በሌላቸው የመንደር አዋላጆች ታግዘው ነበር ይላሉ። አሁን ግን ባላቸው የሴቶች አደረጃጀት፤ በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችና በሌሎች ሞያተኞች እገዛ ጭምር ነፍሰ ጡር እናቶች ከእርግዝና ቀን ጀምሮ ክትትል እንደሚያደረጉ እራሳቸውን ዋቢ በማድረግ ተናግረዋል።

በጤና ተቋም እንዲወልዱ በመደረጉም “እናት ደህና ልጅም ጤና”  እንዲሆኑ አስችሏል።

“ወላጆቼ ዘጠኝ ልጆች ቢወልዱም እኔ በአራት ልጆች አቁሜያለሁ” ያሉት ደግሞ የደገም ወረዳ የቄሲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ባልቻ ገዝሙ ናቸው። በቀበሌአቸው የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላለፉት አስር አመታት መሰጠቱ የቤተሰባቸውን ብዛት ለመመጠን የተሻለ እድል እንደፈጠረላቸው ያስረዳሉ።

“ልጅ አለማብዛትና ከገቢ ጋር አመጣጥኖ በሁለትና ሶስት ዓመታት ልዩነት አራርቆ መውለድ በልጅ አስተዳደግና በእናትየዋ ጤና ላይ ያለውን ጠቀሜታም ተረድቻለሁ” ይላሉ።

ወይዘሮ እልፌ ጐሹ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በአቅራቢያቸው የጤና ተቋማት መስፋፋታቸው የግልና የአካባቢ ጤናቸውን ለመጠበቅ እንዳስቻለአቸው ጠቁመው በተለይ ለሶስት ሕፃናት ልጆቻቸው የፀረ ስድስት ክትባት በቀላሉ እንዲያገኙና በሽታን ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሮ በቀለች ባህሩ በግራር ጃርሶ ወረዳ በወርጡ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ናቸው ። እርሳቸውና ሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው በዋናነት በግልና በአካባቢ ንፅህና፣በእናቶችና ህጻናት ጤና፣ በተላላፊ በሽታዎች ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በድንገተኛ የሕክምና እርዳታ ላይ አተኩረው ሕብረተሰቡን  ከመስተዳደር አካላት ጋር በመሆን እያገዙ መሆኑን ያስረዳሉ።

በተለይ እናቶች የወሊድ ቁጥጥርና የሕፃናት ክትባትን ጨምሮ ነፍሰ ጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋም በማምጣት እንዲገለገሉ የበኩላቸውን ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ የእለት ተእለት ተግባራቸው ነው። ታዲያ ! ስራቸውን የሚያከናውኑት በፍቅር ሲሆን ህብረሰተቡን በማገልገላቸውና ተጨባጭ ውጤት እያዩ በመሆናቸው ደስታ ይሰማቸዋል።

ሞዴል የጤና ኤክስቴንሽን አርሶ አደሮችን በማሰልጠን መሰረታዊ የበሽታ መከላከል ግንዛቤ እንዲጨምርም ስልጠናዎች ሰጥተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በግራር ጃርሶ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ እሸቱ ንጉሴ የጤና ኤክስቴንሽን ኘሮግራሞች ካለፉት 13 ዓመታት ጀምሮ በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች ተግባራዊ መደረጉን ይገልፃሉ።

የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ሙያተኞችን በማሰልጠንና አስፈላጊ መድህኒቶችን በማቅረብ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ነፍሰ ጡር እናቶች በጤና ተቋም እንዲገለገሉ ከመንግስትና ከነዋሪዎች ጋር በመሆን ቤት ለቤት ሕዝቡን የማስተማር ስራ እቅድ ወጥቶበት እየተሰራ ነው ባይ ናቸው።

በግንዛቤ እጥረትና በጤና ተቋማት አለመኖር ሳቢያ ሊሞቱ የሚችሉ እናቶችንና ሕፃናትን ሕይወት ማዳን እንዳስቻለም የሚናገሩት ምክትል ሃላፊው በወረዳው አንድ ቤተሰብ በአማካይ ሰባት ልጆች ይወልድ  ነበር። አሁን ግን  የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የልጆች መጠነ መውለድ ወደ አራት ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

አቶ አስፋው ደፋሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ናቸው። በዞኑ 13 ወረዳዎችና 2 ከተሞች የእናቶችና ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ የተለያዩ ኘሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ መሰነባበቱን ይገልፃሉ።

ኘሮግራሞቹ በአብዛኛው የእናቶችና የሕፃናት ሞትን ለመቀነስ የሚረዱ የጤና ተቋማት ማስፋፋትን ጨምሮ በጤና ተቋማት እንዲገለገሉ ግንዛቤ መፍጠርን የሚያካትት ነው።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ በ63 የጤና ጣቢያዎች ፣ በ3 ሆስፒታሎችና በ321 የጤና ኬላዎች በሚሰጠው አገልግሎት የዞኑ የጤና ሽፋን 96 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።

በ2008 ዓ.ም 56 በመቶ የነበረው በጤና ጣቢያ የሚወልዱ እናቶች ሽፋን በ2009 ዓ.ም ወደ 72 በመቶ ከፍ እንዳለም ይገልፃሉ።

ከአምስት ዓመት በፊት ከ45 በመቶ የማይበልጠው የቤተሰብ ምጣኔም በአሁኑ ወቅት 97 በመቶ ላይ ደርሷል። የክትባት ሽፋኑም ወደ 96 በመቶ ከፍ ብሏል።

የጤና አገልግሎቱን ለማሳደግ በተለይም የእናቶችና ሕፃናት ጤና ለማሻሻል ከዞን ጀምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መስራታቸው ለውጤታማነቱ ምክንያት እንደሆነም ያስረዳሉ።

በመፀዳጃ  ቤት ዝግጅት ፣  በንጽህና አጠባበቅ እንዲሁም በአመጋገብ ስርዓት ዙሪያ በዞኑ የሚያበረታታ ለውጥ ተገኝቷል የሚል እምነት አላቸው ።

እናቶች በጤና ተቋም የመውለድ ፍላጐታቸው እየጨመረ ቢመጣም በአንዳንድ አካባቢዎች የአምቡላንስ ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ፣ የውሃ፣ የመንገድና የሕክምና መሳሪያዎች እጥረት እንዳሉ ጠቁመው ይኸን ለመፍታት የሚያስችሉ አሰራሮችም ከክልሉ ጋር በመነጋገር ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ጥረቱ መልካም ውጤቱም ተስፋ ሰጪ ነው። ነገር ግን በተመዘገበው ስራ መዘናጋት የለብንም ። ለበለጠ ስኬት የተሻለ እውቀትና ተነሳሽነት ጨምረንበት ከተረባረብን ጤናማ ማህበረሰብ የመገንባት ግባችን መሳካቱ አይቀርምና እንበርታ !።