አደጋን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን በአደጋ ጊዜ የሚወጣውን ኃብት ለልማት ማዋል ይገባል- ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ

70
አዲስ አበባ  ጥቅምት  3 /2012  በኢትዮጵያ አደጋን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን በአደጋ ጊዜ የሚወጣውን ኃብት ለልማት ማዋል እንደሚገባ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ተናገሩ፡፡ ኮሚሽነሩ ይህንን የተናገሩት ዓለም አቀፍ  የአደጋ ስጋት ቀን  ‹‹ለአደጋ የማይበገር አቅም እንገባ ›› በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በተከበረበት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። አቶ ምትኩ እንዳሉት በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ በሚያስችሉ የቅድመ መከላከል ተግባራት ላይ በትኩረት በመሥራት አደጋን መቀነስ ይገባል። በአደጋ ቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ማተኮርና አደጋዎች ከደረሱ በኋላም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሰው ህይወትንና ንብረት ከመታደግ ባሻገረ ጉዳቱ እንዲያገግብ በሚል የሚወጣውን ገንዘብ ለማዳንና ለሌሎች የልማት ተግባራት ለማዋል ያግዛል ሲሉም ገልፀዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ለዚህ ተግባር ትኩረት መስጠት እንዳባቸው ነው ያሳሰቡት። ድርቅና ጎርፍ በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰቱ ዋነኛዎቹ የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው። ይህንን ችግር  ለመቀነስ  የቅድመ መከላከል፣ በአደጋ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን እንዲያገግሙና መልሶ የማቋቋም ተግባር ይከናወናል ሲሉ አቶ ምትኩ ተናግረዋል። በእሳት አደጋ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም መንግሰት በአገር ዉስጥ የሌሉትን  የእሳት አደጋ ማጥፊያ ሄሊኮፕተርና አዉሮፕላን ከዉጭ አገር ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም