በአዲስ አበባ በሚገኙ 223 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ይሆናል

255
ጥቅምት 3 / 2012  በአዲስ አበባ በሚገኙ 223 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ እንደሚሆን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ በብሔራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የ2012 ዓ.ም የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብርን በይፋ ማስጀመራቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። መርሃ ግብሩ 300 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና በ223 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ለኢዜአ ገልጸዋል። በ2011 ዓ.ም የምገባ መርሃ ግብሩ 70 ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ አውስተው ባለፈው ዓመት የነበረው መርሃ ግብር በበቂ ሁኔታ ተደራሽ አይደለም ይህም በተማሪዎች አብሮነት ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው በሚል ቅሬታ መነሳቱን ተናግረዋል። ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ በመስጠት የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ዘንድሮ ወደ 300 ሺህ ተማሪዎች እንዲያድግ መወሰኑን ገልጸው የዘንድሮው መርሃ ግብር አብዛኛውን ተማሪ ያሳተፈ መሆኑን ጠቁመዋል። ለምገባ መርሃ ግብሩ የሚያስፈልገው በጀት ለሁሉም ትምህርት ቤቶች እንደተሰጠ ምክትል ሃላፊው ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ትምህርት፣ ጤና ፣ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ትምህርት ቤቶችና ሱፐርቫይዘሮች መርሃ ግብሩን በቅንጅት የሚከታተሉበት አሰራር መዘርጋቱንም አቶ ዘላለም ገልጸዋል። በተጨማሪም ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድ የቅንጅት አሰራር፣ ቁጥጥርና ክትትል ላይ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገም አመልክተዋል። በአዲስ አበባ ደረጃ የምገባ መርሃ ግብሩ በመምህራኖች እንደተጀመረና ከተማ አስተዳደሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የምገባ መርሃ ግብር መጀመሩን አስታውቀዋል። በመርሃ ግብሩ ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል። በዘንድሮው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ላይ ከ10 ሺህ በላይ እናቶች ምግቡን በማቅረብ ስራ ላይ ተሰማርተው የስራ እድል እንዲያገኙ እንደሚደረግም ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም