የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሶሊ ኒኒስቶ ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ

574

ጥቅምት 3 / 2012 የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሶሊ ኒኒስቶ ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።
የ71 ዓመቱ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የሶሊ ኒኒስቶ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል በፕሬዚዳንት ደረጃ የሚካሄድ የመጀመሪያ ጉብኝት ነው ተብሏል።

ጉብኝቱ ፕሬዚዳንቱ እ.አ.አ 2012 ወደመንበረ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአፍሪካ አገር የሚያደርጉት የመጀመሪያው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ እና ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ይወያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሶሊ ኒኒስቶ ከኢትዮጵያ መንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ ነገ ጥቅምት 4 ቀን 2012 ዓም በአዲስ አበባ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤና በሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ላይ ይሳተፋሉ።

ፕሬዚዳንቱ በተከታዩ ቀን ደግሞ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር የሚያወያዩ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያዘጋጁትን የምሳ ግብዣ ይታደማሉ።

ሶሊ ኒኒስቶ በዛው ቀን የሐምሌ 19 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ከትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ጋር በመሆን የሚጎበኙ ሲሆን በትምህርት ቤቱ ካሉ የወላጅ መምህራን ጥምረት አባላት እና ከትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር ይወያያሉ።

በተጨማሪም ሶሊ ኒኒስቶ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ እንደሚተክሉም ተገልጿል።

የሐምሌ 19 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በፊንላንድ መንግስት ድጋፍ ከሚደረግላቸው ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነው።

ከፕሬዚዳንቱ ጋር ከሚመጡ ልዑካን መካከል የፊንላንድ የልማት ትብብርና የውጭ ንግድ ሚኒስትር ቪሌ ስኪናሪ እንደሚገኙበትም በኢትዮጵያ የፊንላንድ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1959 ነው።

ፊንላንድ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን እ.አ.አ በ1965 የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ በፊንላንድ ርዕሰ መዲና ሄልሲንኪ የቆንስላ ጽህፈት ቤት ቢኖራትም ከፊንላንድ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የምታደርገው በስዊድን ስቶክሆልም በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ነው።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ ልማታዊ ትብብራቸው የጀመረው እ.አ.አ በ1967 ሲሆን ፊንላንድ በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና ጤና አጠባበቅ፣ ትምህርት፣ የገጠር ልማትና ሌሎች የልማት መስኮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ በልማቱ መስክ ካላቸው ለረጅም ጊዜ የቆየ ትብብር በተጨማሪ በየዓመቱ የፖለቲካ ምክክር የሚያደርጉበትም መድረክ አላቸው።