በበልግ ዝናብ እጥረት ያጣነውን ምርት በመኸር ለማካካስ ጠንክረን እየሰራን ነው - የአንኮበር ወረዳ አርሶ አደሮች

281
ደብረ ብርሃን ሰኔ 10/2010 በበልግ ዝናብ እጥረት ያጡትን ምርት በመኸር ለማካካስ  በትኩረት እየሰሩ መሆኑን በሰሜን ሽዋ ዞን የአንኮበር ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ። በአንኮበር ወረዳ መሃል ወንዝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሙ ሀብተማሪያም በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ የካቲት ይጀምር የነበረው ዝናብ ዘግይቶ በመጣሉ በበልግ ወቅት ለማልማት ያቀዱትን አንድ ሄክታር መሬት ማልማት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። ይህንንም ለማካካስ በተያዘው መኸር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀም ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴና ማሽላ ሰብሎችን ለማልማት የእርሻና የዘር ስራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በአሁን ወቅትም ጊዜውን ጠብቀው የዘሩት የቆሎና ማሽላ ቡቃያ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ቡቃያውን ከአረም የማፅዳት ስራም ከወዲሁ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። በዚሁ ወረዳ የሀራምባ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጌታቸው አበባዬሁ በበልግ ለማልማት ያቀዱት ስላልተሳካላቸው በተያዘው የመኸር ወቅት ሁለት ሄክታር ማሳቸውን በስንዴ፣ ማሾ፣ ጤፍ፣ በቆሎና ምሰር ዘር ለመሸፈን በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀምም ማሾና በቆሎ ዘርተው ቤተሰቦቻቸውን በማሳተፍ የአረም ስራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሰሜን ሽዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሽፈራ በበኩላቸው በበልግ እርሻው ከሚለማው መሬት ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ቢታቀድም በተከሰተው የዝናብ እጥረት የታሰበው መሬት በዘር ባለመሸፈኑ የሚገኘው ምርት ከግማሽ በታች መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በበልግ እርሻ የታጣውን ምርት በመኸር ለማካካስ አርሶ አደሩን ግንዛቤ በማስጨበጥ በዘር የመሸፈን ስራ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። በተያዘው የመኸር ወቅት 509 ሺህ 816 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብል ዘር በመሸፈን ከ16 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴም 22 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡ በየወረዳውና ቀበሌው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም አርሶ አደሩን በቅርበት በማገዝ እቅዱ እንዲሳካ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም