በአሶሳ የቫት ነጋዴዎች አቅምን ባላገናዘበ ግብር ተቸግረናል አሉ

704

አሶሳ ኢዜአ ጥቅምት 03 / 2012 ዓ.ም  ለአገር እድገት ጠንካራ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ወሳኝ መሆኑን ብንገነዘብም የፍትሃዊነት መጓደል ግን ለኪሳራ እየዳረገን ነው ሲሉ በአሶሳ ከተማ የሚገኙ ቫት ከፋይ ነጋዴዎች ቅሬታ አሰሙ ።
በአሶሳ ከተማ የተሸከርካሪ መለዋወጫ ሱቅ ባለቤት አቶ አህመድ ካሳሁን በሰጡት አስተያየት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የቫት ተመዝጋቢ ሆነው ሲሰሩ ቆይታል፡፡

ካፒታላቸውን ሳይፈቅድ ወደ ቫት ተመዝጋቢነት ተገደው በመግባታቸው ለ67 ሺህ ብር ኪሳራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል ።

በርካታ አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ከግብር ሰብሳቢ  መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነትና ትውውቅ የቫት ተመዝጋቢ ሳይሆኑ ደካማ እቅም ያለን ግን አለአግባብ እንድንጨነቅ እያደረጉን ነው ብለዋል ።

አሻጥረኞቹ ነጋዴዎች እቃቸውን በድብቅ በመጋዘን አስቀምጠው በትንንሽ ሱቆች እንደሚሸጡም አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል፡፡

አብዛኛው ህብረተሰብ ከቫት ከፋዮች ይልቅ ግብር ከማይከፍሉ ነጋዴዎች በቅናሽ ዕቃ እንደሚገዙ ገልፀው የቫት ጠቀሜታን በሚገባ ለማስረፅ የከታታይ የግንዛቤ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል ።

የቫት ተመዝጋቢ መሆን ለንግዱ ማህበረሰብ የሚያስገኘው ጠቀሜታ እንዳለ የሚናገሩት ደግሞ አቶ መኮንን መላኩ የተባሉ ሌላው የቫት ተመዝጋቢ ናቸው፡፡

ይሁንና ግብር አስከፋዩ መስሪያ ቤት በቫት ተመዝጋቢዎች ላይ የሚጥለው ዓመታዊ ግብር አቅምን ያላገናዘበና ግምትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሃገር ያለግብር አታድግም የሚሉት አስተያየት ሰጪው ሰርተን የምንለወጥበትና የሃገሪቱን ልማት የሚያስቀጥል ፍትሃዊ የግብር አጣጣል ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አቶ አሸብር ረጋሳ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት በዚህ ዓመት ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን ገቢን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በግብር ላይ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ከመቀየር ጀምሮ አቤቱታ ካሰሙ ነጋዴዎች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩችን ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል ፡፡

አቅም እያላቸው የቫት ተመዝጋቢዎች ያልሆኑ ነጋዴዎች መኖራቸውን ባለስልጣኑ መረጃ እንዳለው ጠቅሰው በዚህ ዓመት የንግድ ውድድድሩን ፍትሃዊ ለማድረግ በሚከናወኑ አቅጣጫዎች ችግሩ ምላሽ ያገኛል ብለዋል፡፡

በተለይ በአሶሳ ከተማ ከ150 የሚበልጡ ደረሰኝ የማይቆርጡ፣ ትክክለኛ ገቢአቸውን የሚሰውሩና ሌሎችንም ጥፋቶች የሚፈጽሙ ነጋዴዎች እንዳሉ ከንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ መድረሱን ጠቅሰዋል፡፡

ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሆን የታክስ ኦዲት በማድረግ ችግሮችን የማስተካከል እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ አሸብር ገልፀዋል ።

በተለይ ለምስጉን ግብር ከፋዮች ማበረታቻና እውቅና የመስጠት አሰራር በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ 19 ሺህ የሚሆኑ ገብር ከፋዮች መኖራቸውንም ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል ።