የአክሱም ኃውልት ለአደጋ መጋለጡን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ

189
አክሱም ኢዜአ ጥቅምት 3 / 2012 -ለአክሱም ኃውልት ፈጣንና ተገቢ ጥገና ባለመደረጉ ቅርሱ አደጋ ተጋርጦበታል ሲሉ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ። ኃውልቱ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ቅርስ ቢሆንም ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ በኩል ትኩረት እንደተነፈገው ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለድርሻ አካላት እንዳሉት ጥንታዊ የአክሱም ስልጣኔ ልዩ መገለጫ የሆኑ ጥንታዊያን ቅርሶች በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ስለሆነ ተገቢ ጥገና ሊደረግላቸው ይገባል። የአክሱም አስጎበኚዎች ማህበር አስተባባሪ አቶ ጉዕሽ አሰፋ እንዳሉት የአክሱም ኃውልት የመውደቅ አደጋ ተደቅኖበት ይገኛል። በዓለም ቅርስነት የሚታወቁና የቱሪስቶች መዳረሻ የሆኑት የአክሱም ኃውልቶች፣ ጥንታዊቷ የአክሱም ከተማና በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ነባር የጥበብ ውጤቶች እንዲሁም ባህላዊ ቤቶች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ጉዕሽ እንዳሉት መንግስት ችግሩን ተረድቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የአክሱም ኃውልትን ጨምሮ አደጋ የተጋረጠባቸውን ቅርሶች ሊታደግ ይገባል። የአክሱም ዓለም አቀፍ ቅርሶች ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋይ በበኩላቸው እንዳሉት በአክሱም የሚገኙ ጥንታዊያን ኃውልቶች እና የአክሱማዊያን የህንጻ ጥበብ የሆኑ ቅርሶች አፋጣኝ ጥገናና እንክብካቤ ይሻሉ። በተለምዶ ዓዲ-ክልተ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚገኙና የአክሱማዊያን የጥበብ መገለጫ የሆኑ ስፍራዎች ከመጥፋታቸው በፊት በመንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። በአክሱምና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶችን በተመለከተ ለዓለም አቀፍ የቅርስ አስተዳደር በየጊዜው ሪፖርት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በቅርሶቹ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ በኩል ኃላፊነታቸው እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቅርቡ ለተወካዮችና ለፌደሬሽን ምክር ቤቶች ንግግር በዳረጉበት ወቅት በዓመቱ ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ትኩረት እንደሚሰጥ መናገራቸው ተገቢ መሆኑንም አቶ ሚኪኤለ ገልጸዋል። የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹም በበኩላቸው፣ ለቅርሶቹ ጥገና በከተማው አስተዳደር አቅም የሚሰሩ ሥራዎችን በመለየት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ታይቷል፤ የጥገና ሥራውን የሚያከናውኑ አካላት በአካል ተግኘተው አስፈላጊ ግብአቶችን የመለየት ሥራ እያከናወኑ ነው" ሲሉም ገልጸዋል። የጥገና ሥራው ይጀምራል ከተባለ ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆነው ያስታወሱት ኃላፊው፣ ጥገናውን የሚከታተለው የፌዴራል መንግስት አሁን የጀመረው ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የጥንታዊ አክሱም ስነህንጻ እና ሌሎች የአካባቢው ቅርሶች ጥገናና እንክብካቤ ሥራ ከከተማ መስተዳድሩ አቅም በላይ ስለሆነ የክልሉና ፌዴራል መንግስታት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ገብረመድህን አመልክተዋል። ለአክሱም ኃውልትና መካነመቃብር ጥገና ሙሉ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የቅርሶቹ ጥገና ስራ ግብረሀይል አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ምሁር ፕሮፌሰር ተክላይ ሐጎስ ናቸው። የቅርሶች ጥገና አማካሪ ድርጅት እና ጥገናውን የሚያከናውን ሥራ ተቋራጭ ቅርሶቹ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በሟሟላት ላይ እንደሆኑና የጥገና ስራውም በአንድ ወር ውስጥ ይጀምራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ለዋናው የጥገና ሥራ የሚያስፈልግ በጀት መመደቡንና ተቋራጩ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ እየተጠበቀ ስለመሆኑ ቀደም ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ መዘገቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም