የህግ የበላይነትን ለማስፈን ኅብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል -አስተያየት ሰጪዎች

387

ጥቅምት 3 ቀን 2012 በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስፈን መንግስትና ኅብረተሰቡ የግልና የተናጠል ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተገለጸ።

መንግስት በሕዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፈ ህጋዊ ስርዓት ለማስፈን የፍትህ ተቋማቱን አደረጃጀት መፈተሽና አሰራሩንም መገምገም ይኖርበታል።

በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን ከሚያደርጉት በዋነኛነት ጥቅማቸው የተነካባቸው ቡድኖች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በአቋራጭ ለመክበር በመንግስት መዋቅር ስር የሚገኙ አካላት መሆናቸውን ይገለጻል።

እነዚህን የህብረተሰቡን ሰላም እየነሱ ያሉትን አካላት አደብ ለማስገዛት ታዲያ መንግስትና ህዝቡ በተናጠልና በጋራ ያላቸውን ሚና ለይተው በተገቢውና በተቀናጀ መልኩ መወጣት እንዳለባቸው ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው ሰዎች የሚያነሱት።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ደረጄ መርሻ እና ወይዘሮ ወንጌል ታምሬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ መንግስት ብቻውን ያለ ኅብረተሰቡ ተሳትፎ ህግ ማስከበር ይከብደዋል።

በኢትዮጵያ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት እንዲችሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር  የህግ የበላይነትን ማስፈን አለበት ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኖች፣ ወላጆች ፣ ወጣቶች ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሃላፊነትን መወጣት ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም ብለዋል።

መንግስት ህብረተሰቡ በህግ ማስከበር እንዲያግዘው በቅድሚያ የህዝብ ተመራጭ መሆኑን አውቆ ህዝብ የሚለውን መስማት እንደሚኖርበትም አክለዋል።

“ኅብረተሰቡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን ህግ ይከበር የሚል ጥያቄ አለው፤ ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ምላሽ ከሰጠ ከመንግስት ጎን ይቆማል ነው” ያሉት።

ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ለአገሩ ሰላም የበኩሉም ሚና የመወጣት ግዴታ እንዳለበትም ተናግረዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።

የህግ የበላይነት እንዲኖር መንግስት የፍትህ አካላትን ተከታትሎ ትክክለኛና ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ እንዳለበትም በማከል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የኑሮ ውድነትም የሰላምና የደህንነት እንቅፋት መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ “የኑሮ ውድነት ጣራ ሲደርስና ገበያው በህገ ወጥ ደላሎች ሲጥለቀለቅ መንግስት የዳር ተመልካች ከመሆን ፈጣን እርምጃ መውሰድ እዳለበትም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀትን በምሳሌነት ያነሱት ሻምበል ጥላሁን ተርፌሳ፤ በአስሩም የክፍለ ከተማ መምሪያዎች የሚገኙ ፖሊሶች ህግን ለማስከበር የተመደቡበት ቦታ ሳይሆን የለበሱትን የደንብ ልብስ ማሰብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አንድ ፖሊስ ወይም የጸጥታ አካል ወንጀል ተፈጽሞ ሲያገኝ “ይህ የኔ የስራ ቦታ አይደለም” ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ በጸጥታ አስከባሪነቱ ህግ ማስከበር አለበትም ብለዋል።

መንግስትም እነዚህን መሰል የፍትህና የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን እንደገና በማየትና በመፈተሽ አደረጃጀታቸውና አሰራራቸውን ማስተካከል አለበት ነው ያሉት።