ከጅግጅጋ እስከ ሃርሞካሌ የ104 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከጅግጅጋ እስከ ሃርሞካሌ የ104 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ጥቅምት 3 ቀን 2012 ከጅግጅጋ ከተማ እስከ ሃርሞካሌ መገንጠያ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ፡፡ ለመንገድ ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ የውል ስምምነት የተፈረመ ሲሆን ላለፉት ዘጠኝ ወራትም የግንባታ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱ ተመልክቷል፡፡ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ትናንት በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ እንደተገለጸው ከጅግጅጋ እስከ ሃርሞካሌ መገንጠያ የሚገነባው መንገድ 104 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። መንገዱ ከድሬዳዋ እስክ ደወሌ ከተሰራው የክፍያ መንገድ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን ቀደምሲል ከጅግጅጋ ተነስቶ በሐረር-ደንገጎ በኩል 202 ኪሎ ሜትር የነበረውን ጉዞ ወደ 99 ኪሎ ሜትር ይቀንሳል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ የመንገድ ግንባታ ፕሮጅክቱ ከመንግስት በተመደበ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚሰራ ተናግረዋል። አዲስ የሚገነባው መንገድ ከጅግጅጋ ተነስቶ ቱሊ ጉሌድ፣ ሎወናጂ፣ ዱልዓድ፣ ሰመካብ፣ ሃርሙካሌ የተባሉ አምስት የወረዳና የቀበሌ ከተሞችን የሚያገናኝ ነው። ግንባታውን የሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ "የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን" ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን የሚያከናው ደግሞ "ኤስ.ጂ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" ነው፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስተፌ ሙሀመድ በገንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ፕሮጅክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የተሳለጠ የትራስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል። በተለይ ለአካባቢው አርሱ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የሰብል እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶቻቸው ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ በማስቻልም የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። "በክልሉ በተለይ በገጠርና በከተማ ያሉ የእድገት ማዕከላትንና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ሀብቶች ያሉባቸውን አካባቢዎች በመንገድ ልማት ለማስተሳሰር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል" ያሉት ደግሞ የክልሉ መንገድና ትራስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር አብዲቃድር በሽር ናቸው። ከፍተኛ የሆነ ንግድ እንቅስቃሴ የሚከናወነባት ጅግጅጋ ከተማ ተነስቶ ንግድም ሆነ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ቀዳም ሲል በነበረው ፒስታ መንገድ የአካባቢው ማህበረሰብ ለከፍተኛ የትራስፖርት ችግር ይጋለጥ እንደነበረም ያስታወሱት ደግሞ ህገር ሽማግሌ አቶ ሙህየዲን አህመድ ናቸው። በስነ ስርዓቱ ላይ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎችና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።