ሰንደቅ ዓላማ የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን መከላከል እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ

501

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 3/2012 ሰንደቅ ዓላማ የግንኙነት መለያ እንጂ የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን መከላከል እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ ።

ፕሬዚዳንቷ በየዓመቱ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የሰንደቁን ክብር መመለስ መቻል እንዳለበትም ገልፀዋል።

12ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ በመከበር ላይ ነው።

የዘንድሮው የሰንደቅ ዓለማ ቀን  የሚከበረው “ሰንደቅ ዓላማችን የብዝሀነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል ነው።

የሰንደቅ ዓለማ ቀን ጥቅምት በገባ የመጀመሪያው ሰኞ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሆኖ እንዲከበር በተወሰነው መሰረት ነው በዛሬው እለት እየተከበረ ያለው።

በዓሉ በተለይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በተሰናዳ ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በሰንደቅ ዓላማ ረዥም ታሪክ ካላቸው አገራት ተርታ እንደምትሰለፍ ገልፀዋል።

ሰንደቅ ዓላማ ትላንትን፣ ዛሬንና ነገን በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቷ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ልዩነቶች ቢኖሩም የዘር፣ የሀይማኖትና የአስተሳሰብ ልዩነቶችን በጋራ የያዘ መሆኑን የሚያሳይ እንድምታ እንዳለውም ነው ያመለከቱት።

ስንደቅ ዓላማ የሉኣላዊነት መገለጫ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ  ሰንደቅ ዓላማ በየትኛው ቦታ ሲውለበለብ አካባቢው ላይ የአገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር ተቋም አለ ማለት ነው  ብለዋል።

“እኔ ያደግኩባት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልም ሆነ ሲወርድ እንኳን እግረኛ ቀርቶ ተሽከርካሪዎች ይቆማሉ፣ ተሳፋሪዎችም ወርደው ከበሬታቸውን የሚገልፁበት ጊዜ ነበር” ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ለሰንደቅ ዓላማ ይሰጥ የነበረውን ክብር አውስተዋል።

በመሆኑም ይህ በየዓመቱ የሚከበረው በዓል የሰንደቅ ዓላማ ክብር የሚመልስ መሆን መቻል እንዳለበት ነው ፕሬዚዳንቷ ያስገነዘቡት።

ለሰንደቁ የሚሰጠው ከበሬታ በሁሉም ቦታዎች ሊሰጥ እንደሚገባ በማሳሰብ።

ሰንደቅ ዓለማ የግንኙነት መለያ እንጂ የፖለቲካ መሳሪያ እንዳይሆን መከላከል እንደሚገባ የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለአዲሱ ትውልድም የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም ማስተማር እንደሚገባ ገልፀዋል።

የሰንደቅ ዓላማን አያያዝ የሚደነግጉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የሰንደቅ ዓላማን ክብር መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዋነኛ ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ የክልሎች መለያ ባንዲራዎች በሚውለበለቡበት ቦታ ሁሉ ከፍ ብሎ እንዲታይ ማድረግ እና ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀዋል።

የተቀደደ፣ ቀለሙ የለቀቀ ፣ ያረጀ ሰንደቅ ዓላማ አገሪቱንም ሆነ ዜጎቿን የማያስከብር በመሆኑ ዜጎች ለሰንደቅ ዓላማ ልዩ ክብርና ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“የኩራትና የአንድነት መለያ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ለዘላለም ከፍ ብሎ ይውለብለብ” በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።