ኬንያዊቷ አትሌት ብሪግድ ኮስጌይ የሴቶች የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን ሰበረች

69
ኢዜአ ጥቅምት 3/2012  ኬንያዊቷ አትሌት ብሪግድ ኮስጌይ በእንግሊዚቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ለ16 ዓመት ተይዞ የቆየውን የሴቶች የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰንን በቺካጎ ማራቶን ሰብራለች። በውድድሩ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አባብል የሻነህና ገለቴ ቡርቃ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል። በአሜሪካ 42ኛው የቺካጎ ማራቶን ትናንት ተካሄዷል። ብሪግድ ኮስጌይ 2 ሰአት ከ14 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ በመግባት ከእ.አ.አ ከ2003 ጀምሮ በእንግሊዛዊቷ አትሌት ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በ1 ደቃቃ ከ24 ሴኮንድ አሻሽላለች። ፓውላ ራድክሊፍ በለንደን ማራቶን 2 ሰአት ከ15 ደቂቃ ከ25 ሴኮን በመግባት የያዘችው የዓለም ክብረ ወሰን ለ16 ዓመታት ማንም ሳይደፍረው ቆይቶ የነበረ ቢሆንም ኬንያዊቷ አትሌት ክብረ ወሰኑን መስበር ችላለች። በውድድሩ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አባብል የሻነህና ገለቴ ቡርቃ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በወንዶች ውድድር ኬንያዊው አትሌት ላውረንስ ቼሮኖ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ደጀኔ ደበላና አሰፋ መንግስቱ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ያገኙ ሲሆን የዓለም ክብረ ወሰን የሰበረችው ብሪግድ ኮስጌይ ተጨማሪ የ75 ሺህ ዶላር የጉርሻ ሽልማት አግኝታለች። በቺካጎ ማራቶን ለተሳተፉ ተወዳዳሪዎች በአጠቃላይ የ803 ሺህ 500 ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የቺካጎ ማራቶን በዓለም አቀፉ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም