“የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት የአፍሪካውያን ሽልማት ነው” አፍሪካውያን አምባሳደሮች

861

ኢዜአ ጥቅምት 3/2012  ተቀማጭነታቸውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ ለውጥ እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር የተሰጠ እውቅናና የአፍሪካውያን ሽልማት ነው ብለዋል።

አምባሳደሮቹ ትናንት በኢትዮጵያ ኤምባሲ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይን መሸለም በማስመልከት ባደረጉት ዝግጅት የኖቤል ሽልማቱ ለኢትዮጵያ የሚመጥን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

ሽልማቱ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ያኮራ እና አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት መቻላቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር እና የአፍሪካ አምባሳደሮች ዲን አምባሳደር በየነ ርእሶም በበኩላቸው ዶ/ር አብይ የሁላችንም ኩራት ናቸው ብለዋል።

አምባሳደር መለሰ አለም ሽልማቱ ለአፍሪካውያን የተሰጠ እንደሆነ ገልጸው አፍሪካውያን ላሳዩት ድጋፍና ወገንተኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመጨረሻም አምባሳደሮቹ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን እንኳን ደስ አላቹ ብለዋል።