የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸነፈ

740

ኢዜአ ጥቅምት 2/2012የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር(ቻን) ከሩዋንዳ ጋር ላለበት ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ዛሬ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 0 ተሸንፏል።

ስድስተኛው የቻን ውድድር ጥር 2012 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን አገራትም የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም በሩዋንዳ ኪጋሊ 30 ሺህ ሰው በሚያስተናግደው የአማሆሮ ብሔራዊ ስታዲየም የቻን ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።

ለዚህም የመልስ ጨዋታ ዝግጅት ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ 1 ለ 0 ተሸንፏል።

ለግብጹ አል ኢትሀድ አሌክሳንድሪያ ክለብ የሚጫወተው የ26 ዓመቱ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኢማኑኤል ኦክዊ በ19ኛው ደቂቃ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ እንደሚያመራም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የሚጫወተውና በአሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ የሚሰለጥነው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታውን ነገ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ያደርጋል።

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት የሩዋንዳ አቻውን ካሸነፈ በካሜሮን በሚካሄደው የቻን የእግር ኳስ ውድድር ተሳትፎውን ያረጋግጣል።

በካሜሮን ለሚካሄደው ውድድር በሰባት ዞኖች ተከፍሎ ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማጣሪያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

በሁለተኛው ዙር በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 15 ብሔራዊ ቡድኖችና አዘጋጇ አገር ካሜሮን በድምሩ 16 ቡድኖች በቻን ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።

የቻን እግር ኳስ ውድድር በአገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚደረግ ውድድር ነው።