''ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተበረከተው ሽልማት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰጠ ትልቅ ክብር ነው''ም/ር/መ ሙስጠፌ

91
ጅግጅጋ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ''ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተበረከተው ሽልማት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰጠ ትልቅ ክብር ነው'' ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ሽልማት በማግኘታቸው ''የእንኳን ደስ አልዎ!'' ሰልፍ በጅግጅጋ ስታዲዬም ዛሬ ተካሂዷል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት "ሰዎች 50 ዓመታት ስልጣን ላይ ቆይተው የማያገኙትን ዓለም አቀፍ ሽልማት ክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በማግኘታቸው እጅግ ተደስቻለሁ" ብለዋል። ሽልማቱ ለዶክተር ዐቢይ አህመድ የተሰጠው ለዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር ግጭት ለማስቆም ባደረጉት ጥረት፣ የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ አመራሩ በሰላምና በትብብር እንዲሰሩ በጎ ሚና በመጫወታቸው መሆኑንም አመልክተዋል። ዶክተር ዓቢይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምባቸው የነበሩ እስር ቤቶች እንዲዘጉ በማድረግ፣ በኅብረተሰቡ ላይ የነበረው የፀጥታ ስጋት እንዲወገድ ማድረጋቸውን  አውስተዋል። በሰልፉ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች ''ዶክተር ዓቢይ የአፍሪካ የሰላም አባት!"፣ ዶክተር ዓቢይ የለውጥና የአንድነት መሪ ናቸው!'' ፣''ዶክተር ዓቢይ ሽልማቱ ይገባዋል!'' የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማት ያገኙት ባለፈው ዓርብ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም