የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በቀጣዩ አመት ሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ይጀምራል

76
አዳማ ሰኔ 10/2010 የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በቀጣዩ አመት ሁለተኛ  ዲግሪ የትምህርት ፕሮግራም ለመጀመር መዘጋጀቱን አስታወቀ። አካዳሚው የስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው አገር አቀፍ አውደ ጥናት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሐስ ወልደማሪያም ለኢዜአ እንዳስታወቁት በመዲናዋ በአመራር ረገድ ያለውን የትምህርትና ስልጠና ፍላጎት መሰረት በማድረግ የማስተርስ ዲግሪ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል። በአካዳሚው አዲስ የሚከፈቱት የ2ኛ ድግሪ የትምህርት ፕሮግራሞችም በከተማ አመራርና አስተዳደር፣ ኢኮኖሚና ልማት እንዲሁም ኧርባን ሶሉሽንና ዲፕሎማሲ የትምህርት መስኮች መሆናቸውን አስታውቀዋል። የትምህርት መስኮቹ የከተማዋን አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች የሥራ አመራር ብቃታቸውን ለማጎልበትና አቅማቸውን ለመገንባት ያስችላል ብለዋል። አካዳሚው ባለፉት ዓመታትም ለ7 ሺህ 500  የአስተዳደሩ አመራርና ለሌሎችም አስፈፃሚ አካላት የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ስልጠና ሰጥቷል። በአዲስ አበባ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ገብረ ምሩፅ በበኩላቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ 20 ዩኒቨርስቲዎች ልምድ በመውሰድና የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የስርዓተ ትምህርት ቀረጻው መካሄዱን ጠቅሰዋል። የተመረጡት የስልጠና መስኮቹ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት የሚችል፣ የከተማን ውስብስብነትና ስነ ልቦና የተረዳ ጠንካራ የከተማ አመራር ለመፍጠር ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል። ትምህርቱን ለመጀመር የሚያስችሉ የሰው ሃይል፣ የመፅሀፍት፣ የቤተመጸሐፍትና የኮምፒውተር ላብራቶሪ ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተጀመረው የአካዳሚው ዋና ጊቢ ህንፃ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንም ዶክተር ገብረ  አስታውቀዋል። የስልጠና ፕሮግራሙንም በጥር ወር 2011 ዓ.ም ለማስጀመር መታቀዱን የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ማተበ ታፈረ ''በአካዳሚው የተቀረጸው ስርዓተ ትምህርት የሀገሪቱን የአመራር ክፍተት የለየ ነው'' ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ከተሞች እያደጉ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ከተሞችን የሚመጥን አመራር አላፈራንም ያሉት ዶክተር ማተበ በዚህ ረገድ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የትምህርት መስኮቹ አስፈላጊ ናቸው። በኢትዮዽያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳንኤል ሊሬቦ በበኩላቸው ''በአዲስ አበባ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ ከመምራትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አንፃር ድክመት አለ'' ብለዋል። አካዳሚው የአመራሩን የእውቀት፣ ክህሎትና የአመለካከት ክፍተት ለመሙላት በሚያስችል መልኩ ስርዓተ ትምህርት መቅረጹ ለከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ጥቅም የሚፈጥርና የተሻለ የመልካም አስተዳደር ለማስፈን ይረዳል ብለዋል። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከፖሊሲ ጥናት ማዕከልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ምሁራን፣ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም