የጎዳና ተዳዳሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል የሠላም ተሸላሚ በመሆናቸው ደስታቸውን ገለፁ

85
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 2/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኖቤል የሠላም ሽልማት በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ በአዲስ አበባ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ገለፁ። በታላቁ ቤተ መንግስት የተገነባው የአንድነት ፓርክ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይና በምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች ባለፈው ሐሙስ ተመርቆ ስራ ጀምሯል። ይህን ተከትሎ ፓርኩ በክፍያ ሲጎበኝ የመክፈል አቅም የሌላቸው ዜጎች ሳይጎበኙት እንዳይቀሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅድሚያ እነዚህ ዜጎች እንዲጎበኙት አድርገዋል። በዚሁ መሰረት ትናንት ከአንድ ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ኑሯቸውን በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጎዳናዎች ላይ ያደረጉ ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል የሠላም ሽልማት በማሸነፋቸው ደስታቸውን ገልፀዋል። በፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ ጎዳና ላይ ህይወቷን የምትገፋው ወጣት ቃልኪዳን ሙሉጌታ ዶክተር አብይ የኖቤል የሠላም ሽልማት ማሸነፋቸው ሲነገር ደስታ እንደተሰማት ገልጻለች። ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የሚኖረው ወጣት ኪሩቤል ተስፋዬም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ኩራት ነው ብሏል። የቀድሞ ሠራዊት አባል የነበሩትና አሁን ጎዳና ላይ እየኖሩ ያሉት አቶ ተስፋዬ አበበም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሸለሙ ምክንያት የሆነው በአገራቸው ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በስራ በመትጋታቸው ነው ብለዋል። ያገኙት ሽልማት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካን ህዝብ የሚያኮራ በመሆኑ ሁሉም ሊደሰት ይገባል ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሠላምና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀ የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሠላም እንዲፈታ ተነሳሽነት በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሠላም ተሸላሚ ሆነዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም