በተፈጠረልን የሥራ ዕድል ተጠቅመን ኑሮአችንን ለማሻሻል እንጥራለን-የድሬዳዋ ከተማ ምግብ ዋስትና ተጠቃዎሚች

69
ድሬዳዋ ጥቅምት 2 ቀን 2012 መንግሥት በፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቅመው ኑሮአቸውንና ሕይወታቸውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት ውጤት እንዳስገኘላቸው በከተማ ምግብ ዋስትና መርሃ ግብር የተጠቀሙ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ። በድህነት ውስጥ የሚገኙ ከ43 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአስተዳደሩ የከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ገልጿል፡፡ በከተማ ምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በመርሐ ግብሩ በሚያደርጉት ተሳትፎ ሕይወታቸውን እየቀየረው ነው። የስድሳ ዓመቱ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ሰሞኑን በተጀመረው ሶስተኛ ዙር የከተማ ምግብ ዋስትና መርሐ ግብር ተጠቃሚ ከሆኑት 15 ሺ 600 የድሃ ድሃ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የስምንት ልጆች አባት መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ኢብራሂም፣  የጉልበት ሥራ በመስራት ይተዳደሩበት የነበረው ሂደት ተቀይሯል፡፡ ‹‹አሁን የጉልበት ሥራ መጣ ጠፋ እያልኩኝ መጨነቅ ትቻለሁ፤ የእኔም ፣ የቤተሰቤም ተስፋ ለምልሟል'' ብለዋል:: ተመሣሣይ ሃሳብን ያንፀባረቀው ወጣት ሻረው ተካ በጎዳና ሕይወታቸው ከመሠረቱ ጓደኞቹ ጋር በሥራው መሰማራቱን ይናገራል፡፡ ‹‹እንደምታየው የከዚራን የቆሸሹ ጎዳናዎች በማፅዳት የቀድሞ ንጽህናውን እየመለስን ነው። ሠርቶ መብላት ያስደስታል። መንግሥት ይህን መሰል ዕድል ቢፈጥር ረብሻና ብጥብጥ የሚወገድ ይመስለኛል›› ብሏል፡፡ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በዚህ ሥራ የምናሳልፍ በመሆኑ ከምናገኘው ገንዘብ በመቆጠብ ወደ  አነስተኛ ሥራ በመግባት ኑሮአችንና ሕይወታችንን ለማሻሻል መትጋት ጀምረናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፈቲሃ ዑመር ናቸው፡፡ በመርሐ ግብሩ በቀጥታ ድጋፍ ከተደረገላቸው አረጋውያን መካከል የ75 ዓመቱ አቶ ዘለቀ አሰፋ ‹ተስፋ በቆረጥሁበት ወቅት መንግሥት ስለደረሰልኝ አመሰግናለሁ›› ብለዋል፡፡ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሽብሩ በበኩላቸው በፅዳት ሥራ በመሰማራት ገቢ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሥራ ዕድሉ ራሴን ካገለልኩበት ማጀት ወደ አደባባይ እንድወጣና ከሌሎች ጋር እንድቀላቀል ያስቻለኝ በመሆኑ ተስፋዬ ለምልሟል›› በማለትም ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ለሥራው የሚያገለግሉና ለደህንነት መጠበቂያ የሚሆኑ መሣሪያዎች እንዲሟላላቸው ጠይቀዋል፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሴፍትኔት ሥራዎች ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ንጉሴ ባለፉት ሶስት ዓመታት በከተማው 43 ሺ 610 የድሃ ድሃ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 7ሺህ የሚጠጉ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በቀጥታ እንዲደገፉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ ዮናስ ገለፃ የመርሐ ግብሩ ተጠቃዎች በአካባቢ ጥበቃ ፣ በመሠረተ ልማትና በደረቅ ቆሻሻ ማፅዳት ፣አካባቢን አረንጓዴ በማልበስና በመፀዳጃ ቤቶች ግንባታ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ከተማዋን ውብና ፅዱ እያደረጉ ናቸው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ያለባቸውን የምግብ ክፍተት ከመሙላት በተጨማሪ የሥራ ባህላቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ንም ገልጸዋል፡፡ ለመርሐ ግብሩ ማሰፈጸሚያ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንና ተጠቃሚዎቹ ከሚያገኙት ገንዘብ 20 በመቶውን ቆጥበው በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ መርሐ ግብር ታቅፈው ቀጣይ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ከመርሃ ግብሩ የሚሰናበቱት የመጀመሪያ ዙር ተጠቃሚዎች መካከል 3423ቱ ወደ አነስተኛ ሥራ የሚያሻግራቸው ሥልጠና በመረጡት የሥራ መስክ  ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል። የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፤ ብድርም እንደሚመቻችላቸው አስረድተዋል፡፡ ሰሞኑን ሥራ ለጀመሩት 15 ሺ 610 ሰዎች ለሥራ የሚያገለግሏቸው ያልተሟሉ መሣሪያዎች እንደሚሟላላቸውም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም