የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ

አዳማ ኢዜአ ጥቅምት 2 /2012፡-የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፋቸው የተሰማቸው ደስታ ዛሬ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ገለጹ። በተመሳሳይ በአምቦ፣ ጅማ፣ ድሬደዋና ጭሮ ከተሞች በተካሄደው ሰልፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በአዳማ ነዋሪዎቹ ድጋፋቸውን የገለጹት የኢፌዴሪንና የክልሉን ሰንደቅ ዓላማን አንግበው የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመሩትን ለውጥ ለመደገፍ ከጎናቸው እንቆማለን ሲሉ ሰልፈኞቹ ባሰሙት መፈክር ገልጸዋል። የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በስደት ላይ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመልሰው በሃሳብ እንዲሞግቱ ያደረጉ ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና ወንድማማችነትን በማስፈን የለውጥ ኃይል በመሆናቸው ለሽልማት እንዳበቃቸው ተናግረዋል። በተለይ ይህ እድል ለህዝቡ ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ በመደመር እሳቤ አንድነቱን ይበልጥ እንዲያጠናክር ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል። በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ኑሩ አበጀሃድ በሰጠው አስተያየት ለዶክተር አብይ አህመድ የተሰጠው የኖቤል የሰላም ሽልማት የመደመር ፍልስፍና ውጤታማነትን የሚያሳና አለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንደሚያመልክት ተናግሯል፡፡ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀማድ በሳሙት ንግግር “ ለዶክተር አብይ የተሰጠው የኖቤል ሽልማት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው” ብለዋል፡፡ ሽልማቱ በከተማውም ሆነ በሀገሪቱ እኩልነት በማሰፍን ለህዝቦች ተጠቃሚነት ሁሉም ጠንክሮ እንዲሰራ ብርታት እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አምቦና አካባቢዋ ነዋሪዎች በፈረስ ጉግስና በሞተር ብስክሌት በመታጀብ ባካሄዱት ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍና የተሰማቸውን ደስታቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት እንደግፋለን ፣ የመደመር ፍልስፍናን እናጠናክራለን ሲሉም ባሰሙት መፈክር አስታውቀዋል፡፡ የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ቱፋ አብዲ “አሁን ያገኘነውን ሰላም ብናስቀጥል የበለጠ ሽልማት እናገኛለን፤፡ ስለዚህ አንድነታችንን ካጠናክረን ከማሸነፍ የሚያግደን የለም “ብለዋል፡፡ በድሬደዋ እና ጭሮ ከተሞች የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ በመግለጽ ከጎናቸው እንደሚቆሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም