የኢትዮጵያ ቮሊቦል የዳኞች ሙያ ማህበር ተቋቋመ

69
ጥቅምት 1/2012 የኢትዮጵያ ቮሊቦል የዳኞች ሙያ ማህበር የምስረታ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተደርጓል። የቮሊቦል የዳኞች የሙያ ማህበር ሲቋቋም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነውም ተብሏል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ የሙያ ማህበሩ መቋቋም ለቮሊቦል ስፖርት ዕድገትም ሆነ ስፖርቱን በዳኝነት ለሚመሩት አካላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በቮሊቦል ታሪክ በአገር አቀፍ ደረጃ "የዳኞች የሙያ ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመ ነው" ያሉት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ማህበሩ በቀጣይ ራሱን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል የዳኞች ሙያ ማህበር መተዳደሪያ ደንብ በዝርዝር ቀርቦ ሰፊ ውይይት እንደተደረገበትና የማሻሻያ ሃሳቦችም ከጉባኤው ተሳታፊዎች ተሰጥቶ የማህበሩ መተዳደርያ ደንብ በሙሉ ድምጽ መጽደቁም ተመልክቷል፡። በምስረታ ጉባኤው ላይ የሙያ ማህበሩን የሚመሩት ሰባት የስራ አሰፈጻሚ አባላት የተመረጡ ሲሆን በዚሁ መሰረት ኢንስትራክተር ፍርድያውቃል ደቻሳ ከአዲስ አበባ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል። በተጨማሪም ኢንስትራክተር ያሬድ ታደሰና ወይዘሮ ሰላማዊት ባሉ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ኢንስትራክተር ወንድማገኝ ሃይለስላሴ ከኦሮሚያ ክልል፣ አቶ ሲሳይ ውቤ ከደቡብ ክልል፣አቶ ሰለሞን ገነቱ ከአማራ ክልል እና ወይዘሮ አዜብ ክዳኔ ከትግራይ ክልል የቮሊቦል ዳኞች የሙያ ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባላት ሆነው በጉባኤው ተሳታፊዎች ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ማህበሩ እንዲመሰረት ላደረጉት ድጋፍ የለሰለሰ ድጋፍ በጉባኤው ተሳታፊዎች ምስጋና ማግኘታቸውን የስፖርት ኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም