በአፋር 9ሺህ 371 ሄክታር ሰብልና እጽዋት ከበረሀ አንበጣ ነጻ ተደረገ

115
ጥቅምት 1/2012 በአፋር ክልል በ9ሺህ 371 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው ሰብልና እጽዋት ከበረሀ አንበጣ መንጋ ጥቃት ነጻ መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። በክልሉ ያለው ዝናባማ የአየር ጠባይና የግንዛቤ ማነስ የአንበጣ መንጋውን የመቆጣጣር ሂደት አዳጋች ያደረገው መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገልል ። የግብርና ሚነስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዮስ ሰላቶ ለኢዜአ እንደገለፁት ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ  በክልሉ የተከሰተውን የበረሀ አንበጣ የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ ነው ። በክልሉ ስምንት ወረዳዎች በ41 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደ ቅኝት 14 ሺህ ሄክታሩ በአንበጣ መንጋ መጠቃቱ ታውቆ የቁጥጥር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል ። የቁጥጥር ስራው በሰውና በሄሊኮፕተር በታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል ። በአንበጣ መንጋው ከተጠቃው መሬት ውስጥ በ9 ሺህ 371 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልና እጽዋት ነጻ መደረጉን ጠቅሰዋል ። በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ውብአንተ ግርማ በበኩላቸው በክልሉ የአንበጣ መንጋው የተከሰተባቸው ወረዳዎች ከፍተኛ የእንሰሳት መኖ ያለባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል። በክልሉ ያለው ዝናባማ የአየር ጠባይ ለአንበጣው መራባት በፈጠረው አመቺ ሁኔታ የቁጥጥር ስራውን አዳጋች ከማድረጉም በላይ የመንጋው ስርጭት እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁመዋል ። በተጨማሪም ህብረተሰቡ በከብቶች ላይ ጉዳት ያስከትላል በሚል የኬሚካል ርጭቱ እንዲካሄድ ፈቃደኛ አለመሆን ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል ። ጭፍራ ወረዳ መንጋው ከተከሰተባቸው 19 ቀበሌዎች ውስጥ በስድሰቱ ብቻ ርጭቱ መካሄዱን ለአብነት ጠቅሰዋል ። እንደ ባለሙያው ገለጻ በወረዳዎቹ የሚገኙ አመራሮች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨመጥ ለቁጥጥር ስራው መሳካት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። አፋር ክልል እንስሳት፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳትና እጽዋት በሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድኑር መሃመድ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ስራውን በግብዓትና በበጀት በመደገፍ የመካከሉ ስራ ወጤታማ እንዲሆን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በየደረጃው የሚገኘው አመራር ከማህበረሰብ መሪዎች ጋር በመሆን  ህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋሉ የአመለካከት ክፍተቶችን የማረም፣ የማስተማርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እንዲያከናውን አቅጣጫ ተይዞ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ። የበረሀ አምበጣ መንጋ አፋርን ጨምሮ በሱማሌ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ውስጥ ከወራቶች በፊት መከሰቱ ይታወቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም