የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ትምህርት ቤቶችን ጎበኙ

93
ደሴ ኢዜአ ጥቅምት 1/2012 ዓም  በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ የመሰረተ ልማትና የአስተዳደር ሰራተኞች አለመሟላት በመማር ማተማሩ ሒደት ላይ ጫና ማሳደሩን የወረዳው መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ተናገሩ። የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የ2012 የትምህርት አጀማመርና እንቅስቃሴ አስመልክቶ  በደሴ ዙሪያና አልቡኮ ወረዳዎች የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የህዳሴ 2ተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሀመድ አበበ እንደገለቱት 700 የሚጠጉ ተማሪዎች እየተማሩ ቢሆንም በመብራት መቋረጥ ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ የፕላዝማ ትምርት ማስተማር አለመቻሉን ተናግረዋል። የመብራት ችግሩን ጀኔሬተር በመጠቀም ለመፍታት ቢሞከርም በዓመት ከ120 ሺህ ብር በላይ ወጪ በመጠየቁ ከ30 በለይ የአይሲቲ መማሪያ ኮምፒተሮች ያለ አገልግሎት ተቀምጠዋል ። በዚህም ተማሪዎች ተገቢውን እውቀት እንዳያገኙና ብቁ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባለፈ በትምህርት ጥራቱ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ የቤተ መጽሀፍ ባለሙያ ፣ መጽሃፍ የሚያሰራጭ፣ ጽዳት፣ መዝገብ ቤትና ማህደር፣ የጥበቃ ኃይልና ሌሎችም አስፈላጊ የአስተዳደር ሰራተኞች አለመኖራቸዉም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የክፍሎች አቧራ፣ ያአረጁ ክፍሎት አለመጠገን፣ የአጥር፣ ዉሃና መብራት ችግር ማስተማሩ ላይ ብቻ እንዳናተኩር አድርጎናል ያሉት ደግሞ የጭረቻ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አራጋዉ መሀመድ ናቸዉ፡፡ ከስድስት በላይ የአስተዳደር ሰራተኛ ስለሚያስፈልግ እንዲቀጠርልን ብንጠይቅም በጀት የለም በሚል እስካሁን አንድም ባለመኖሩ መምህራን ደርበዉ እንዲሰሩ መገደዳቸውንና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል ። የደሴ ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኡስማን ሙህዲን በበኩላቸዉ ቀደም ሲል በበጀት እጥረት ምክንያተ የድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች አለመቀጠራቸውን አስታውሰው በዚህ ዓመት 10 ሰራተኞችን ለመቅጠር በጀት ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል። የመብራት ችግሩን ግን ከአቅም በላይ በመሆኑ ካሉት ሦስት ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ሁለቱ ስለተቋረጠባቸዉ የተግባር ትምህርት እየተሰጠ አይደለም ብለዋል ። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሰዉ ሀብትና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኙ 6 ትምህርት ቤቶችን በመጎብኘት ያሉባቸውን መሰረታዊ ችግሮቻቸውን መለየት እንደቻሉ ተናግረዋል። በምልክታቸዉ የመሰረት ልማት አለመሟላት ፣ የተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ያለመጀመር፣ የመጽሃፍ አያያዝ፣ ቤተ መጽሃፍት ስራ አለመጀመርና ሌሎች ችግሮች መመልከታቸውን ተናግረዋል። እንዲሁም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች 50 በመቶ ብቻ ማለፋቸዉን ታዝበናል ያሉት ወይዘሮ ፋንቱ የችግሩ መንስኤ ተለይቶ መልክ እንዲይዝ ይደረጋል ብለዋል። ችግሮችን በየደረጃዉ በመለየት በዞንና በወረዳ አቅም የሚቀረፉት እዚሁ እንዲቀረፉ የክልል መንግስትን ድጋፍ የሚፈለጉትን ደግሞ በአስቸኳይ መልስ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተናግረዋል ። የምክር ቤቱ አባላቶች በተመለከቷቸዉ ችግሮች ዙሪያ ከደቡብ ወሎ አመራሮች ጋር ነገ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም