በትግራይ ክልል ለጀማሪ መምህራን የተሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ያለፉት 380 ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ለጀማሪ መምህራን የተሰጠውን የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ያለፉት 380 ናቸው

መቀሌ ሰኔ 10/2010 በትግራይ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ከወሰዱ ከ3 ሺህ በላይ ጀማሪ መምህራን መካከል የብቃት መመዘኛውን ያለፉት 380ዎቹ ብቻ ናቸው። በክልሉ መመዘኛውን ላላፉት መምህራን ትናንት በውቅሮ ከተማ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል። በትግራይ ትምህርት ቢሮ የመምህራን ሙያ ፈቃድ ዳይሬክተር መምህር ገብረ ክርስቶስ ከበደ እንዳሉት በክልሉ በዓድዋና ዓብይ ዓዲ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት በዲፕሎማ ደረጃ ሰልጥነው የብቃት ማረጋገጫ ምዘናውን ከወሰዱት 3 ሺህ 500 መምህራን መካከል መመዘኛውን ያለፉት 380ዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ እውቅና የተሰጣቸው ጀማሪ መምህራን በትምህርት አመራር፣ ስነ-ምግባርና በትምህርት ጥራት ላይ አትኩሮ የተሰጠውን የብቃት መመዘኛ ፈተና በማለፋቸው ነው። በክልሉ በሚገኙ 52 ወረዳዎች ተመድበው በማስተማር ላይ ያሉና የብቃት መመዘኛውን ያላለፉ ጀማሪ መምህራን በቀጣይ ዓመት በድጋሚ አጭር የሙያ ስልጠና ወስደው ለፈተና እንደሚቀርቡም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ እንዳሉት መምህራን አገር ተረካቢ ዜጋን የማፍራት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ መምህር የተሰጠውን ከባድ ኃላፊነት በአግባቡ አውቆ ወደ ተግባር መተርጎም እንዳለበት አሳስበዋል። በየአካባቢው የሚገኙ ወላጆችና የወላጅ ከሚቴ አባላትም በየቀኑ የትምህርት ሂደትን ከመምህራን ጋር እየተገናኙ የልጆቻቸው ስነ ምግባርና የትምህርት ሁኔታ መከታተል ይጠበቅባቸዋል። የመምህርነት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ እውቅና ከተሰጣቸው መምህራን መካከል በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን ህንጣሎ ወረዳ የተመደበችና ማየት የተሳናት መምህርት አዜብ ገብረህይወት አንዷ ናት፡፡ መምህርት አዜብ በዚሁ ጊዜ እንዳለችው የአገሩን ታሪክና ቅርስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የበኩሏዋን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ገልፃለች። በትግራይ ማእከላዊ ዞን ታህታይ ማይጨው ወረዳ የኢንግሊዝኛ መምህርት የሆነችው መምህርት ብርሂን ሺሻይ በበኩሏ ተማሪዎች ቋንቋውን በሚገባ አውቀው ለሌሎች ትምህርቶችም አጋዠ እንዲሆናቸው በሚገባቸው መንገድ እንደምታስተምር ተናግራለች።