የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታውን ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል

91
አዲስ አበባ ጥቅምት 1 / 2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር /ቻን/ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ላለበት ግጥሚያ ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር ይጫወታል። ስድስተኛው የቻን ውድድር ጥር 2012 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን አገራትም የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም በሩዋንዳ ኪጋሊ 30 ሺህ ሰው በሚያስተናግደው የአማሆሮ ብሔራዊ ስታዲየም የቻን ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። ለዚህም የመልስ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታል። በአሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ የሚመሩት ዋልያዎቹ ከሩዋንዳ ጋር ላለባቸው ጨዋታ ከመስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በባህርዳር ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር ለሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ ዋልያዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ዛሬ ረፋዱ ላይ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ማድረጋቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በ34 ዓመቱ ሰሜን አየርላንዳዊ አሰልጣኝ ጆናታን ማኪንስትሪ የሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከዋልያዎቹ ጋር ለመጫወት ትናንት ከሰዓት ባህርዳር የገቡ ሲሆን የመጀመሪያ ልምምዳቸውንም ዛሬ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋሉ። ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የነገውን የብሔራዊ ቡድኖቹን የወዳጅነት ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አጠናቆ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ እንደሚያመራም እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ገልጿል። ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የሚጫወተውና በአሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ የሚሰለጥነው የረዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ያደርጋል። ኢትዮጵያና ሩዋንዳ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት የሩዋንዳ አቻውን ካሸነፈ በካሜሮን በሚካሄደው የቻን የእግር ኳስ ውድድር ተሳትፎውን ያረጋግጣል። ዋልያዎቹ ሐምሌ 2011 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የቻን የማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲ አቻቸውን 5 ለ 3 በሆነ ድምር ውጤት ማሸነፋቸውም አይዘነጋም። በካሜሮን ለሚካሄደው ውድድር በሰሜን ዞን፣ በምዕራብ ዞን ኤ፣ በምዕራብ ዞን ቢ፣ በማዕከላዊ ዞን፣ ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን እና ደቡብ ዞን ተከፋፍሎ ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማጣሪያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። በሁለተኛው ዙር በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 15 ብሔራዊ ቡድኖችና አዘጋጇ አገር ካሜሮን በድምሩ 16 ቡድኖች በቻን ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል። የቻን እግር ኳስ ውድድር በአገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚደረግ ውድድር ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም